Fana: At a Speed of Life!

በጉባኤው ላይ የተላለፉት ዐበይት መልዕክቶች

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) 5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የህዝብ ጤና ጉባኤ “የአፍሪካ የጤና ደህንነትና ሉዓላዊነት፤ ከጤና ጥገኝነትና ተጋላጭነት ወደ ባለቤትነትና ጽናት የሚደረግ ሽግግር” በሚል መሪ ሀሳብ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤ የተለያዩ ሀገራት መሪዎችና የተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቁልፍ ባሏቸው ጉዳዮች ላይ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል፡፡
በአጽንኦት ከተነሱ ጉዳዮች መካከል አፍሪካ በራሷ አቅም የጤና ስርዓት በመገንባት የጤና ሉዓላዊነቷን ማረጋገጥ እንደሚገባት እንዲሁም በጉባኤው ለሚወሰኑ ለውሳኔዎች የተባበረ ቁርጠኛ ተግባር እንደሚያስፈልግ የቀረቡ ጥሪዎች ይገኙበታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የአፍሪካን የጤና ስርዓት ለማጠናከር በመደመር እሳቤ አህጉራዊ አቅምንና ጥረቶችን ማስተባበር ይገባል፡፡
በዚህም በትብብርና አህጉራዊ ጥንካሬዎችን በመደመር የአፍሪካን የጤና ስርዓት በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
በሁለንተናዊ የጤና ጉዳዮች ራስን መቻልና የጤና ሉዓላዊነትን ማስጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ፤ የአህጉሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ዲጂታል የጤና መሳሪያዎች በአፍሪካ ተመራማሪዎች ሊመረቱ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ለዚህም የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ ቀጣይነት ያለው በጀትና በራሳችን ሕግ የሚመራ የጤና መረጃ ጥበቃ ሥርዓት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡
የቡሩንዲ ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ኤቫሪስት ንዳይሺሚዬ በበኩላቸው፤ የአህጉሪቱ የጤና ሉዓላዊነት የሚከበረው አፍሪካውያን በዘርፉ መዋዕለ ነዋያቸውን ሲያፈስሱ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በአፍሪካውያን የሚደገፍ ጤና፤ በአፍሪካውያን የሚወሰን የጤና ሥርዓት መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡
የሩዋንዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ንሰንጊዩምቫ ባደረጉት ንግግር፤ የአፍሪካ የጤና ሉዓላዊነት እያንዳንዳችን በተናጠል በምናሳካው ግብ ብቻ ሳይሆን በጋራ በምንገነባው ስኬት ላይ ይወሰናል በማለት ከተናጠል ይልቅ በጋራ የመስራትን አስፈላጊነት ጠቅሰዋል፡፡
የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን በበኩላቸው፤ ቃል ኪዳኖችን ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየርና ሀገራዊ ባለቤትነትን ለማጠናከር እንዲሁም የአፍሪካን የጤና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የሚያስችል አዲስ የጋራ ርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቅርበዋል።
ጉባኤው ከመግለጫዎች ያለፈ ውጤት እንዲያመጣ ተግባራዊ ርምጃዎችን፣ ጠንካራ አጋርነቶችን እንዲሁም በመላው አፍሪካ የሰዎችን ህይወት ለመታደግ አዲስ ቁርጠኝነት እንዲኖር ጥሪ ያቀረቡት ደግሞ የሴራሊዮኑ ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ማዳ ቢዮ ናቸው፡፡
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የህብረተሰብ ጤና ደህንነት የእውነተኛ ሉዓላዊነት መሰረት መሆኑን አንስተዋል፡፡
የአህጉሪቱ ጤና ሥርዓት በውጭ ሀብትና በሌሎች በጀቶች ላይ ብቻ በዘላቂነት መመሥረት ስለማይቻል አፍሪካ ራሷን ለመቻል ተጨባጭ ርምጃዎች መውሰድ እንዳለባት አሳስበዋል።
ሊቀመንበር በንግግራቸው የህዝቧን ጤና መጠበቅ የማትችል አፍሪካ የወደፊት ዕጣ ፈንታዋን ለመቆጣጠር አይቻላትም ሲሉ አስምረውበታል፡፡
በቴዎድሮስ ሳህለ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.