11ኛው የፌደራልና ክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች ጉባኤ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 4 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) 11ኛው የፌደራልና ክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በጉባኤው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እንዳሻው ጣሰው፣ የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነሮችና የአስሩም ክልሎች የፖሊስ ኮሚሽነሮችና ምክትል ኮሚሽነሮች እየተሳተፉ ነው።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው፣ በጉባኤው ላይ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በለውጥ ጉዞ ላይ እደምትገኝ ጠቅሰዋል፡፡
ለውጡን ተከትሎም ለሃገርና ለህዝብ የሚጠቅሙ ተጨባጭ ለውጦች መታየታቸውንም ተናግረዋል፡፡
በአንጻሩ በየጊዜው አጀንዳ እየቀያየሩ የሃገሪቱን ሰላምና ልማት የሚያደናቅፉ የውስጥና የውጭ ኃይሎች በጋራ እና በተናጠል ጥረት እያደረጉ ይገኛሉም ብለዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ይህን ጥረታቸውን ለማክሸፍም የጸጥታ ኃይሎች ውስጣዊ አንድነታቸውን ጠብቀው የሃገሪቱን ሰላምና ጸጥታ እያስከበሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ መሰረት በማድረግ የሃገሪቱንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ያገናዘበ እንዲሁም የህዝብና መንግስት የፖሊስ አገልግሎት ላይ የተመሰረተ ሪፎርም እየተካሄደ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ጉባኤው የፖሊስ ተቋማትን ውስጣዊ አንድነት በማጠናከርና የፖሊስ አባልና አመራርን የመፈጸምና የማስፈጸም ተቋማዊ አቅምን ለማሳደግ የሚረዳ የጋራ አቋም የሚወሰድበትና በሁሉም ክልሎች ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ለመገምገም የሚረዳ ነው ተብሏል፡፡
ጉባኤው ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ይሆናል፡፡
በፋሲካው ታደሰ