Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ባለፉት ሶስት ወራት በ12 ሺህ 37 መዝገቦች ላይ ውሳኔ መስጠቱን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 12 ሺህ 239 መዝገቦች ለውሳኔ ቀርበው በ12 ሺህ 37 መዝገቦች ላይ ውሳኔ መስጠቱን አስታወቀ፡፡

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ የመጀመሪያውን ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም በተመለከተ በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸው ወደ ዐቃቤ ሕግ ከተመሩ መዝገቦች መካከል 33 ሺህ 714 መዝገቦች ላይ በፌደራል ፍርድ ቤቶች ክርክር መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

እንዲሁም በሩብ ዓመቱ 2 ሺህ 480 መዝገቦች የመጨረሻ የፍርድ ቤት ውሳኔ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ በ2 ሺህ 371 መዛግብት ላይ ተከሳሾቹ የጥፋተኛነት ውሳኔ የተሰጠባቸው ሲሆን ቀሪዎች ተከሳሾች በነጻ መሰናበታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ተቋሙ አዲስ አደረጃጀት በመዘርጋት ትኩረት የሚሹ የሥራ ዘርፎችን የሚከውኑ የሥራ ክፍሎችን ማቋቋሙንም ተናግረዋል፡፡

ከዘርፎቹ መካከልም ሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የሚከታተል ዳይሬክቶሬት መቋቋሙን ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም የክልሎችን ቅንጅታዊ አሰራር የሚከታተል እና ድጋፍ የሚሰጥ አዲስ የሥራ ክፍል እንዲሁም የንቃተ ህግ ትምህርን በልዩ ትኩረት የሚሰጥ ዳይሬክቶሬት መቋቋሙን ገልጸዋል፡፡

ከኢኮኖሚ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ጥፋተኞች ተብለው ውሳኔ ያገኙትን ከማስቀጣት በተጨማሪ ሃብታቸውን ይዘው እንዳይቀጥሉ የሚያደርግ ሀብት የማስመለስ ተግባር ላይ አተኩሮ የሚሰራ የስራ ክፍል በአዲስ መልክ ተደራጅቷልም ነው ያሉት፡፡

አዲሱ የስራ ክፍል በሰራው ስራ 412 ሚሊየን ብር የሚገመት ገንዘብ ወደ መንግስት ለማስመለስ በሂደት ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተገናኘ በተለያዩ ቦታዎች በተፈጠረው ሁከት በሰው እና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት በ2 ወራት ውስጥ በቅንጅት የምርመራ ስራ በማከናወን በፌደራል ደረጃ በ114 መዝገቦች ከ3 ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መመስረቱንም አውስተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.