ጠ/ሚ ዐቢይና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ኢትዮ ኢንጅነሪንግን ጎበኙ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 4 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በቅርቡ መዋቅሩን ያሻሻለውን ኢትዮ ኢንጅነሪንግ ቡድንን ጎበኙ።
ኢትዮ ኢንጅነሪንግ ቡድን ያሳየው ለውጥ የሚደነቅ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቢሾፍቱ ቅርንጫፋቸውን ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር በመሆን ጎብኝተናል ብለዋል በፌስቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ።
ቅርንጫፉ ለመከላከያ ሠራዊት እንዲሁም ለንግድ የሚሆኑ ተሽከርካሪዎች የሚገጣጠሙበት ነው ተብሏል።
በተመሳሳይ መሪዎቹ የኢትዮጵያ አየር ኃይልን የጎበኙ ሲሆን በዚህም የቴክኖሎጂ አቅማቸውን እና ዝግጁነታቸውን ተመልክቻለሁ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሃገሪቱን የአየር ክልል በማስጠበቅ እና ድንገተኛ እንዲሁም የተፈጥሮ አደጋዎችን የመሳሰሉ ሁኔታዎች ባጋጠመ ጊዜ ከምድር ጦር ጋር ተባብሮ በመሥራት ብሔራዊ ኩራትነቱን አስመስክሯልም ነው ያሉት፡፡
በጉብኝቱ ላይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።