Fana: At a Speed of Life!

ለ11ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች የሙያ ትምህርት መስጠት ሊጀመር ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 4 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለ11ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች ከቀለም ትምህርት በተጓዳኝ የሙያ ትምህርት መስጠት ሊጀመር መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
 
እስካሁን ተግባር ላይ የነበረው የትምህርት ስርዓት ሙያን መሰረት ያላደረገ በመሆኑ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍልን ካጠናቀቁ በኋላ የከፍተኛ ትምህርትን መቀላቀል ካልቻሉ ተጨማሪ የሙያ ባለቤት የመሆን እድላቸው ጠባብ ነበር።
 
የትምህርት ሚኒስቴር በአዲሱ የትምህርት ስርዓት እንደሚጀምር የገለፀ ሲሆን ይህም ተማሪዎች የሙያ ባለቤት እንዲሆኑ ያግዛቸዋል ተብሏል።
 
በትምህርት ስርዓቱ ተማሪዎች የ11ኛ ክፍልን ሲቀላቀሉ በተፈጥሮ እና ማህበራዊ ሳይንስ ከተመደቡ በኋላ አንዱን የሙያ ትምህርት መርጠው በስሩ የሚገኙትን ኮርሶችን እንደሚማሩ ተነግሯል ።
 
በተፈጥሮ ሳይንስ ስር አምስት የሙያ ትምህርቶች የሚሰጡ ሲሆን እነዚህም የግንባታ፣ የማምረቻው፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ የጤና እና የግብርና ናቸው።
 
በማህበራዊ ሳይንስ ስር ደግሞ የማህበራዊ ሳይንስና ቋንቋ፣ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ እንዲሁም የስነ ጥበብ የትምህርት ዘርፎች መሆናቸው ተጠቁሟል።
 
በዘርፉ የሚሰጡ የሙያ ትምህርቶችን ተማሪዎች ለአራት መንፈቅ አመት ከወሰዱ በኋላ የዘርፉ ጀማሪ ባለሙያ ሆነው ይመረቃሉ።
 
በ2013 ዓ.ም መጨረሻ 850 ሺህ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ትምህርትን ስለሚያጠናቅቁ የሙያ ትምህርቱ በተወሰነ መልኩ በዘንድሮው አመት ይጀመራል ተብሏል።
 
በዚህም በዘንድሮው አመት የ 12ኛ ክፍልን ለሚያጠናቅቁ ተማሪዎች የንድፈ ሃሳብ ትምህርቶችን በመስጠት በክረምት እና በቀጣይ አመት የተግባር ትምህርቱ እንደሚሰጣቸው ተነግሯል።
 
ትምህርቱን ለማስጀመርም የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ የሚገኝ ሲሆን አዲሱ የስርዓተ ትምህርት ለውጥ በ2014 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንደሚሆን ተገልጿል።
 
በሃይማኖት ኢያሱ
 
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.