Fana: At a Speed of Life!

የገዳ ስርአትን በስርአተ ትምህርቱ በማካተት ለማስተማር የተያዘውን እቅድ መተግበር የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የኦሮሚያ ክልል ገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 4 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የገዳ ስርአትን በስርአተ ትምህርቱ በማካተት እንደ አንድ የትምህርት አይነት ለማስተማር የተያዘውን እቅድ መተግበር የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የኦሮሚያ ክልል ገለጸ።

በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፥ ስርአቱን ከጀማሪ እስከ 8ኛ ክፍል ለሚገኙ ተማሪዎች ለመስጠት የመጽሃፍ ዝግጅት ተከናውኗል።

በመጽሃፍቶቹም በኦሮሞ ማህበረሰብ ውስጥ ለዘመናት ሲተገበሩ የኖሩትን የዴሞክራሲ ስርአትን ለመገንባት የሚያስችሉ፣ በሰዎች መካከል በመከባበርና በመዋደድ ለመኖር የሚያግዙና የሰብአዊ መብት እንዲከበር የሚያስገድዱ እሴቶችን የሚያስተምሩ አንጓዎች ተካተዋል ነው ያሉት።

የቦረና ዞን አናሬሮ ወረዳ አባገዳ ጉዮ ጎበቡሌ በበኩላቸው የገዳ ስርአቱን በትምህርት ስርአቱ ውስጥ ማካተቱ የሚከባበር፣ መብትና ግዴታውን የሚረዳና የሚተገብር ሀገሩንና ህዝቡን የሚወድ ትውልድ ለመፍጠር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የኦሮሞ ፎክለር ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ሚልኬሳ ኤደኤና የትምህርት ክፍሉ የ2ኛ ዲግሪ ተማሪ ረሂማ ዘይኑ እንደሚሉትም የገዳ ስርአት በትምህርቱ ውስጥ መካተቱ ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ የሚታዩ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ፋይዳ ይኖረዋል።

እንደሀገርም መሰል ሀገር በቀል እውቀቶችን በመፈተሽና ወደ ትምህርት ስርአቱ በማምጣት ቀጣዩን ትውልድ ማነጽ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

በትእግሰት ስለሺ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.