ኢንጂነር ታከለ ኡማ በሲዳማ ክልል የማዕድን ቁፋሮ የሚካሄድባቸውን ስፍራዎች ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ኢንጅነር ታከለ ኡማ የተመራ ልዑክ በሲዳማ ክልል የማዕድን ቁፋሮ የሚካሄድባቸውን ስፍራዎች በዛሬው እለት ጎብኝቷል።
ኢንጂነር ታከለ በጉብኝታቸው ከሀዋሳ 180 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የገናሌ ወንዝ ገባር በሆነው በሎጊታ ወንዝ ዳር ወርቅ ለማውጣት በሂደት ላይ የሚገኘውን የሲዳማ ጎልድ ማይኒንግ ኩባንያን መመልከታቸውን በፌስቡክ ገፃቸው ባወጡት መረጃ አስታውቀዋል።
ኩባንያው በአካባቢው ተወላጆችና ነዋሪዎች ባለቤትነት የሚመራ እና የሚበረታታ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ የወርቅ ፋብሪካው ከሁለት ወር በኋላ ምርቱን ለገበያ ማቅረብ እንደሚጀምርም ገልፀዋል።
ይሁን እንጅ አካባቢው ከፍተኛ የመንገድና የመሰረተ ልማት ችግር ያለበት በመሆኑ ችግሩን መፍታት በሚቻልበት መንገድ ዙሪያ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ጋር መወያየታቸውንም ገልጸዋል።
በስፍራው ከመሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴርም ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
“የማዕድን ኢንዱስትሪው በሚገባው መጠን እንዲያድግ፣ ዘርፉም ለሃገሪቱ ዕድገት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ቴክኖሎጂና የሰው ዕውቀት በማከል በኢንዱስትሪ ደረጃ እንዲያድግ ማስቻል ይገባል” ብለዋልም ኢንጂነር ታከለ።