ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ጥፋት ፈፅመዋል ባላቸው 77 ተማሪዎች ላይ እርምጃ ወሰደ
አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ጥፋት ፈፅመዋል ባላቸው 77 ተማሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።
በዩኒቨርሲቲው የጥፋት አላማን አንግበው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ጥቂት ተማሪዎች ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲታወክ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።
በመሆኑም የዩኒቨርሲቲውን አጠቃላይ ህልውና ጭምር አደጋ ውስጥ በመክተት የጥፋት ተልዕኮ ሲያከናውኑ ቆይተዋል ነው ያለው።
ተማሪዎቹ ከጥፋታቸው እንዲመለሱና እንዲታረሙ ተደጋጋሚ ምክርና ጊዜ የተሰጣቸው ቢሆንም ከጥፋታቸው ሊታረሙ አለመቻላቸውንም ገልጿል።
በመሆኑም የዩኒቨርሲቲውን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለማስቀጠል፥ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲስተጓጎል ምክንያት ሆነዋል ባላቸው 77 ተማሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን ነው የገለጸው።
እርምጃ ከተወሰደባቸው ተማሪዎች መካከል ሁለቱ ሙሉ ለሙሉ ሲሰናበቱ፥ 75 ተማሪዎች ደግሞ ለሁለት ዓመት ከትምህርት ገበታቸው ታግደዋል።
በተጨማሪም ሁለት መምህራን ተማሪዎችን በማስኮብለል ድርጊት ላይ ተሳትፈው በመገኘታቸው የደመወዝ ቅጣትና የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።
ተማሪዎቹ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስተጓጎል የተለያዩ እንቅፋቶች ከመፍጠር አንስቶ በተደራጀ ሁኔታ ሠላማዊ ተማሪ ላይ ጥቃት በማድረስ፣ ህገወጥ ሠልፍ በማደራጀት እና ትምህርት እንዳይካሄድ የማሸማቀቅ እና የማስፈራራት ተግባር ሲፈጽሙ ነበር ተብሏል፡፡
በተያያዘም የብሔር ግጭት የሚቀሠቅሱ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን ንግግሮች ማድረግ፣ በህገወጥ ሠልፍ የዩኒቨርሲቲው ንብረት ላይ ውድመት ማድረስም ተማሪዎቹ የተሳተፉበት ህገ ወጥ ድርጊት መሆኑም ተገልጿል።
ዩኒቨርሲቲው ድብቅ አላማን አንግበው ተቋሙ የጥፋት ዓላማዎች ማራመጃ እንዲሆን ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የሚሠሩ ተማሪዎች፣ መምህራን እና የአስተዳደር ሠራተኞች ላይ በቀጣይ የማጣራት ሥራ እሰራለሁ ማለቱን ከዩኒቨርሲቲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።