የህወሃት ጁንታ ፈንቲ ረሱ ዞን በንፁሀን አርብቶ አደሮች ላይ በፈጸመው ጭፍጨፋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ ተደረገ
አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 2 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የህወሃት ጁንታ በአፋር ክልል ፈንቲ ረሱ ዞን በንፁሀን አርብቶ አደሮች ላይ በፈጸመው ጭፍጨፋ ጉዳት ደርሶባቸው በዱብቲ ሆስፒታል ህክምና ላይ ለሚገኙ ዜጎች የተለያዩ ምግብና አልባሳት ድጋፍ ተደረገ፡፡
የአፋር ክልል ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ኤይሻ ያሲን በቦታው በመገኘት ድጋፉን አድርገዋል።
ድጋፉን ባደረጉበት ወቅት የህወሃት ጁንታ በንፁሀን አርብቶ አደሮች ላይ የፈፀመው ጭፍጨፋ የአፋር ህዝብ መቼም የማይረሳው ትልቅ በደል ነው ብለዋል ፡፡
በመሆኑም ጁንታው ባደረገው ጭፍጨፋ ጉዳት ደርሶባቸው በዱብቲ ሆስፒታል ህክምና ላይ ለሚገኙ ወገኖች፣ በህወሃት ጁንታው ተገደው ወደ ጦርነት ገብተው ጉዳት የደረሰባቸውና ቆስለው ህክምና በመከታተል ላይ ለሚገኙ ምርኮኞች የተለያዩ ምግብና አልባሳትን ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል ፡፡
ሃላፊዋ ኤይሻ ያሲን ጁንታው “የአፋር ህዝብን ባይሞክርው ይሻለው ነበር የአፋር ህዝብ በኢትዮጵያነቱ የማይደራደር ለወራሪ ሃይልም እጁን የማይሰጥ ጀግና ህዝብ መሆኑን መቼም ከታሪክ ሳይረዳ አይቀርም” ሲሉም ተናግረዋል ፡፡
ጁንታው ከአፋር ምድር ተጠራርጎ እስኪወጣ ድረስም ከክልሉ ልዩ ሀይል እና ህዝብ ጋር በመሆን በቁርጠኝነት እንዋጋለን በርግጠኝነት እናሸንፋለን ማለታቸውን ከአፋር ክልል መገናኛ ብዙሃን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡