Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያዊያን በቤጂንግ 2021 የዓለም ዓቀፍ የሮቦት ውድድር አሸነፉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤጂንግ 2021 የዓለም ዓቀፍ የሮቦት ውድድር ሻምፒዮና ኢትዮጵያዊያን በተሳተፉበት ዘርፍ የወርቅ፣ብር እና ነሀስ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆነዋል።
በፈረንጆቹ መስከረም 13/2021 በቤጂንግ የዓለም ዓቀፍ የሮቦት ውድድር ሻምፒዮና ከ20 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የምርምር ተቋማት፣ ኢንተርፕራይዞች እና 2 ሺህ የሚጠጉ ተወዳዳሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ኢትዮጵያዊያን በተሳተፉበት ዘርፍ የወርቅ፣ብር እና ነሀስ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆነዋል፡፡
ከውድድሩ በተጨማሪም የዘመናዊ ሮቦቶች አውደ ርዕይ ተካሂዷል፡፡
ከምርምር ተቋማት እና ከዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ቡድኖችም በውድድሩ ላይ ዘመናዊ መሣሪያዎቻቸውን አሳይተዋል።
በውድድሩ 2 ሺህ የሚጠጉ ትምህርታቸውን በቻይና ሀገር እየተከታተሉ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች መካከል በቲያንጂን የቴክኖሎጂ እና ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፣በዎርልድ ስኪል ውድድር የቻይና ምርምር ማዕከል ፈጠራ ኢንስቲትዩት እና በሉባን አውደ ጥናት እና ኢፒአይፒ በተባሉት ተቋማት የሚሰለጥኑ ተሳትፈውበታል።
ውድድሩ ለአራት ቀናት በአራት ምድቦች የተካሄደ ሲሆን ፥በተመሳሳይ ሰዓት ከውድድሩ ጎን ለጎን የዓለም ዓቀፍ ሮቦት ኮንፈረንስም ተካሄዷል፡፡
በዘመናዊ ማምረቻ አርቲፊሻል ኢንተለጀንት ማኑፋክቸሪንግ እና በጤና እንክብካቤ ሮቦቶች ትግበራ ላይ ያተኮረው፥ ሮቦቶች ከተለዋዋጭ አካባቢ ጋር መልመድ እና በስራ ሁኔታ ውስጥ ከሰዎች እና ከሌሎች ሮቦቶች ጋር መተባበር ይችሉ እንደሆነ ተፈትሿል።
ኢትዮጵያዊያን በተወዳደሩበት በ ትራይ ኮ ሮቦትስ ኤንድ አፕሊኬሽን / “Tri-Co” Robots and Robot Application/ ዘርፍ፥ እጩ ዶክተር ሰላሙ ይስሃቅ የወርቅ፣የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪው አባኩማ ጌታቸው እና የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ ፀጋዬ አለሙ የብር ሜዳሊያ አግኝተዋል።
በተጨማሪም እጩ ዶክተር ዮሐንስ ኃ/መስቀል እና የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ ሄኖክ ሰይፉ የነሀስ ሜዳሊያ እንዲሁም የዋንጫ ተሸላሚዎች ሆነዋል።
በውድድሩ ላይ የተገኙት የዓለም የሮቦት ውድድር ዝግጅት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ዣንግ ዩዌይ፥ የዓለም ዓቀፍ ሮቦት ውድድር በፈረንጆቹ በ2015 ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሰባተኛው ዙር እንደተካሄደ ገልጸዋል።
በመሆኑም የውድድሩ አጠቃላይ ይዘት እና ስርዓት ቀስ በቀስ እየበለፀገ፣ የፈጠራ ማዕከል እየሆነና እና እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።
በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ለአሸናፊዎቹ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.