Fana: At a Speed of Life!

የምስራቁ አጎራባች ክልሎች የጋራ ኮማንድ ፖስት ስብሰባ በጅግጅጋ ከተማ ተካሄደ።

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዛሬው ዕለት የምስራቅ አጎራባች ክልሎች የጋራ ኮማንድ ፖስት ስብሰባ በጅግጅጋ ከተማ ተካሄደ።

የጋራ ኮማንድ ፖስቱ በወንጀል መከላከል ዘርፍ የተከናወኑ ሥራዎችን ሪፖርት ገምግሞ በቀጣይ መሰራት በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

በመድረኩ ላይ የሶማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መሀመድ አሊ ባቀረቡት ሪፖርት ባሳለፍነው ሣምንት ብቻ በክልሉ በተደረገው የክትትል ሥራ ከ5 ሺህ ግራም በላይ አደንዛዥ ዕፅ፣ ብዛት ያላቸው የስለት መሳሪያዎች፣ ዘመናዊ ባለመነፅር መሳሪያዎች ሲያዙ፣ ህገወጥ የዶላር አዘዋዋሪዎችና የተለያዩ የጥፋት ወንጀሎችን ሊፈፅሙ የሞከሩ ወንጀለኞችም በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ነው የገለጹት፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ፓሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዓለሙ መገራ በበኩላቸው÷ የጋራ ኮማንድ ፖስቱ ጁንታው የህወሓት አሸባሪ ቡድን፣ ኦነግ ሸኔ፣ አልሸባብና በኢኮኖሚ ላይ የህገወጥ ምንዛሬ አሻጥር የሚሰሩ ወንጀለኞች በተለያየ መልኩ የፀጥታ ተግዳሮቶች እንደነበሩ መገምገማቸውን ገልጸዋል።

ኮሚሽነሩ አያይዘውም÷ በቀጣይ በመስቀል በዓል አከባበር፣ በሶማሌና ሐረሪ ክልሎች የሚካሄደውን ምርጫ ብሎም ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ ምንም አይነት የሠላም መደፍረስ እንዳይኖር ኮማንድ ፖስቱ በጋራ አቅጣጫ ማስቀመጡን ተናግረዋል።

ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራባቸው የሚገቡ አካባቢዎችም ተለይተው የተቀመጡ መሆናቸውን ኮሚሽነር ዓለሙ ገልፀዋል፡፡

ዩኒቨርስቲዎች፣ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች፣ የወጪና ገቢ ንግድ ኮሪደሮችና ሌሎች የፀጥታ ችግር ቢፈጠር ተብሎ የተለዩ ቦታዎች ላይ ከማሕበረሰቡ ጋር በመቀናጀት ደህንነት የማረጋገጥ ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

መንግስት ምግብ ነክ የሆኑ ግብዓቶችን ከቀረጥ ነጻ መፍቀዱን ያስታወሰው የጋራ ኮማንድ ፖስቱ የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠር በሕዝብ ላይ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ ከትትል የሚያደርግ እና እርምጃ የሚወስድ መሆኑንም እንዳሳሰበ ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.