ለተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ሁልጊዜም ከፍ ያለ ምስጋና አለው- አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 28 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አንዳንድ የውስጥና የውጭ ኃይላት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ለመጣል ባሰፈሰፉበት ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን ከቆሙት ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በመሆኗ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ሁልጊዜም ከፍ ያለ ምስጋና አለው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ::
በ11ኛው የአፍሪካና የዐረቡ ዓለም አፈ ጉባዔዎችና አቻ ምክር ቤቶች የጋራ ጉባዔ (አሴካ) ላይ የተሳተፉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ከጉባዔው ጎን ለጎን ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የፌዴራል ብሔራዊ ምክር ቤት አፈጉባዔ ሳክር ሆባሽ ጋር ተወያይተዋል::
በጉባዔው ላይ ተሳትፈው ዛሬ ወደ ሀገር ቤት የተመለሱት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፥ ሁለቱ ሀገራት በባህል፣ በታሪክ፥ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፥ በቱሪዝም እና በሌሎች መስኮች የቆየ፣ ጠንካራና መልካም ግንኙነት እንዳለቸው ገልፀው፥ ይህም ግንኙነት ከፍ ወዳለ ወንድማማችነት ደረጃ አድጓል ብለዋል::
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትን አደጋ ላይ ለመጣል አንዳንድ የውስጥና የውጭ ኃይላት ባሰፈሰፉበት ወቅት ሉዓላዊነታችን እና የግዛት አንድነታችን ተጠብቆ እንዲቀጥል ከኢትዮጵያ ጎን ከቆሙት ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በመሆኗ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ሁልጊዜም ከፍ ያለ ምስጋና አለው ብለዋል::
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ለሀገራዊ ምክክር ቅድመ ሁኔታዎችን ጨርሳ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን አካታች ሀገራዊ ምክክር በማድረግ የጠነከረች እና አንድነቷ የተረጋገጠ አገር ለመገንባት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
አፈጉባኤ ሳክር ሆባሽ በበኩላቸው÷ የጠነከረችና የግዛት አንድነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያ እንድትቀጥል የሕዝባቸውና የመንግስታቸው ፅኑ አቋም መሆኑን መግለፃቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በመጨረሻም በሁለቱ ሀገራት መሪዎች እና ሕዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት እጅግ መልካም እና በወንድማማችነት ላይ የተመሰረተ ሲሆን ÷ይህንን ግንኙነት በሁለቱ ሀገራት ምክር ቤቶች ደረጃም አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል ሲሉ ፍላጎታቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!