Fana: At a Speed of Life!

መንግስት በትግራይ የሚኖሩ ዜጎች ከጁንታው ወታደራዊ መሣሪያዎችና ማሠልጠኛዎች እንዲርቁ መልዕክት ማስተላለፉ ለዜጎች የሚሰማውን ኃላፊነት እንደሚያሳይ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥት በትግራይ የሚኖሩ ዜጎች ከሽብርተኛው ህወሓት ወታደራዊ መሣሪያዎችና ማሠልጠኛዎች እንዲርቁ መልዕክት ማስተላለፉ ለዜጎች የሚሰማውን ኃላፊነት የሚያሳይ መሆኑን የቀድሞ ሠራዊት አባል የሆኑት ብርጋዴር ጄነራል ካሳዬ ጨመዳ ገለጹ፡፡

ብርጋዴር ጄነራል ካሳዬ ጨመዳ እንደተናገሩት÷ አሸባሪው ህወሓት ሰሞኑን እያወጣቸው የነበሩ መግለጫዎችና ሲያሰራጫቸው የነበሩ የሐሰት መረጃዎች ቡድኑ ለጦርነት ሲዘጋጅ እንደቆየ በግልጽ የሚያሳዩ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡

በዛሬው እለትም ትምህርት ቤትን ጨምሮ ሌሎች ማህበራዊ ተቋማት ተመቱብኝ ብሎ የውሸት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ሲታወቅበት የኖረውን የሀሰት ባህሪ በማስቀጠል ላይ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ይህን የውሸት ፕሮፓጋንዳውንም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲረዳው ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

“የኢትዮጵያ ሠራዊት ከጥንት ጀምሮ በወታደራዊ ዲሲፕሊን ይታወቃል” ያሉት ብርጋዴር ጄነራል ካሳዬ ጨመዳ፥ ከዚህ አኳያ መንግሥት በትግራይ ክልል የሚኖሩ ዜጎች ከጁንታው ወታደራዊ መሣሪያዎችና ማሠልጠኛዎች እንዲርቁ መልዕክት ማስተላለፉ ለዜጎች የሚሰማውን ኃላፊነት የሚያመላክት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ይሁን እንጂ የሽብር ቡድኑ አሁንም እንደለመደው የሐሰት መረጃ እያሰራጨ ይገኛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በመሆኑም የሽብር ቡድኑን ትክክለኛ ማንነት የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲገነዘበው በማድረግ ረገድ ኢትዮጵያዊያን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ቡድኑ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለሰብዓዊ ድጋፍ ይውል የነበረን 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ መዝረፉም ለሕዝብ ደንታ የሌለውና ተራ ዘራፊ ቡድን መሆኑን በግልጽ የሚያመላክት ነው ብለዋል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ቡድኑን ከማውገዝ ጎን ለጎን የዘረፈውን ነዳጅ እንዲመልስ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.