Fana: At a Speed of Life!

ቆጣሪ እንዲገባላቸው ካመለከቱ ደንበኞች በሐሰተኛ መታወቂያ ገንዘብ ወስዷል የተባለ ተከሳሽ በ18 ዓመት እስራት ተቀጣ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመብራት ቆጣሪ እንዲገባላቸው ካመለከቱ ስምንት ደንበኞች ሐሰተኛ የተቋም መታወቂያ በማሳየት “ለኤሌትሪክ ሥራ” በሚል ገንዘብ ወስዷል የተባለ ተከሳሽ በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እና 20 ሺህ ብር ተቀጣ።

የቅጣት ውሳኔውን ያሳለፈው በኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ነው።

የኦሮሚያ ክልል የፍትሕ ቢሮ የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ፤ አበበ ዋለ በተባለ ተከሳሽ ላይ የሙስና ወንጀልን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ንዑስ 3 እና የኢነርጂ አዋጅ ቁጥር 810/2006 አንቀጽ 28 ንዑስ ቁጥር 1 ሥር የተመላከተውን ድንጋጌ መተላለፉን ጠቅሶ በዘጠኝ መዝገቦች ክስ አቅርቦበታል።

ተከሳሹ ካልተያዙ ሁለት ግብረ-አበሮቹ ጋር በመሆን በሸገር ከተማ ለገጣፎ ለገዳዲ ክፍለ ከተማ ደንበል ጣፎ ወረዳ የኤሌትሪክ አገልግሎት ሠራተኛ ሳይሆን ሐሰተኛ የተቋም ሠራተኛ መታወቂያ አንገቱ ላይ በማንጠልጠል፣ በተቋሙ ስም ተመሳስሎ የተሠራ የገንዘብ መሰብሰቢያ ደረሰኝ ከታኅሣስ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ቆጣሪ እንዲገባላቸው ለኤሌትሪክ አገልግሎት ካመለከቱ ስምንት ደንበኞች ቤት በመሄድ “የኤትሪክ አገልግሎት ሥራ እሠራለሁ” በማለት 92 ሺህ 999 ብር መቀበሉ በክስ ዝርዝሩ ተመላክቷል፡፡

ገንዘብ ተቀብሎ ሊሰወር ሲልም የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ ባደረገው ክትትል በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ፍርድ ቤት ቀርቦ የተመሰረተበት ክስ እንዲደርሰውና በንባብ እንዲሰማ ተደርጓል።

ተከሳሹ የወንጀል ድርጊቱን ክዶ መከራከሩን ተከትሎም ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግን የሰውና የሠነድ ማስረጃ በመስማት መርምሮ ተከሳሹ በተከሰሰበት ድንጋጌ ሥር እንዲከላከል ብይን ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት በመያዝ ተከሳሹ በቀረቡበት ሁሉም ክሶች ጥፋተኛ ነው በሚል በ18 ዓመት ጽኑ እስራትና 20 ሺህ ብር እንዲቀጣ ወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.