በ3ኛ ዙር ወደሀገራቸው ለሚገቡ የ2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን የሚደረገው አቀባበል ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሦስተኛ ዙር ወደሀገራቸው ለሚገቡ የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን የሚደረገው አቀባበል መጀመሩ ተገለጸ፡፡
“Leave your Legacy, savor your holiday” የሚል ስያሜ በተሰጠው በዚህ በሶስተኛው ምዕራፍ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን የእረፍት ጊዜያቸውን ተጠቅመው በሀገር አቀፍ ደረጃ በተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አማካኝነት ዐሻራቸውን እንደሚያኖሩ ይጠበቃል፡፡
በተጨማሪም የተቸገሩ ወገኖቻቸውን የሚያገዙበት፣ የቀሰሙትን ትምህርትና ልምድ ለወገኖቻቸው የሚያሸጋግሩበት እና የተለያዩ የቱሪስት መስህቦችን በመጎብኘትና በመዝናናት መልካም ትውስታን ይዘው የሚመለሱበት የማጠቃለያ ምዕራፍ መሆኑተገልጿል፡፡
ይህ ምዕራፍ እስከ መስከረም አጋማሽ ይቆያል መባሉን የቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያየ ዓለም ለሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን እንዲጎበኙ ባደረጉት ጥሪ መሰረት በሁለት ዙሮች በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መምጣታቸው ይታወቃል፡፡