ለልደት በዓል ወደ ቅዱስ ላልይበላ የሚመጡ እንግዶችን በተሳካ መንገድ ለማስተናገድ ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የልደት በዓልን በደብረ ሮሃ ቅዱስ ላልይበላ ለሚያከበሩ እንግዶች መስተንግዶውን የተሳካ ለማድረግ በቂ ዝግጅት ማድረጉን የላልይበላ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል።
የከተማ አስተዳደሩ ታላቁን በዓል ለማክበር ዝግጅት አድርጎ እንግዶችን እየተቀበለ መሆኑንም ገልጿል።
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የላልይበላ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ማንደፍሮ ታደሰ፥ የኢየሱስ ክርስቶስና የቅዱስ ወ ንጉሥ ላል ይበላ የልደት በዓል በደብረ ሮሃ ቅዱስ ላል ይበላ በተለየ ድምቀት እንደሚከበር ገልፀዋል።
ከተማ አስተዳደሩም ለዚሁ በዓል ግብረ ኀይል በማቋቋም ወደ ሥራ መገባቱንም የጠቆሙት ሃላፊው፥ ለበዓሉ ለየት ያለ ዝግጅት ማድረጉን አንስተዋል።
የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የባንክ እና ሌሎች አገልግሎቶች መጀመራቸውንም ጠቅሰው ፥ሆቴሎች እንግዶችን በመልካም መስተንግዶ ለመቀበል ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
የእንግዶች ሰላም የተጠበቀ እንዲሆን ሁሉን አቀፍ ዝግጅት ተደርጓልም ነው ያሉት።
በአሸባሪው ቡድን ጉዳት የደረሰበት የላል ይበላ አየር ማረፊያ የአካባቢውን ቱሪዝም ለማነቃቃት መንግሥት ባደረገው ልዩ ትኩረት ሥራ እንዲጀመር መደረጉንም አስታውቀዋል።
ከደብረ ሮሃ ቅዱስ ላል ይበላ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት በተጨማሪ በዙሪያው ያሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች ለጎብኚዎች ክፍት እንዲሆን መሠራቱንም አስታውቀዋል።
እንግዶች ምንም አይነት የፀጥታ ችግር አለመኖሩን ተረድተው ሳይሰጉ ወደ ላል ይበላ መጥተው በዓሉን እንዲያከብሩም ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!