Fana: At a Speed of Life!

የመጀመሪያው ብሔራዊ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባዔ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመጀመሪያው ብሔራዊ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባዔ በአዲስ አበባ ተካሄደ፡፡

ጉባዔው “በይነ መረብ ለአካታች ልማት” በሚል መሪ ሀሳብ ነው በአካል እና በኦንላይን ጥምረት የተካሄደው፡፡

በጉባዔው ላይ÷ ከበይነ መረብ ጋር ተያይዞ ያሉ ዕድሎች እና ፈተናዎችን በሚመለከት የተነሱ ሀሳቦች ተንሸራሽረውበታል፡፡

በተጨማሪም የመረጃ መረብ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥቅሞቹ፣ ተደራሽነቱ ተመጣጣኝ እና ትርጉም ያለው ስለመሆኑ፣ የበይነ መረብ ተደራሽነት እና መሠረታዊ መብቶች የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች በጉባዔው ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ከበይነ መረብ ጋር ተያይዞ የሚመጡ አሉታዊ ጫናዎችን ለመቋቋምና ዜጎች በበይነ መረብ የሚያደርጉት ግንኙነት አስተማማኝ እንዲሆን የሚያስችሉ ልዩ ልዩ አዋጆች በሥራ ላይ እንዲውሉ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ ዓመት በኢትዮጵያ የሚካሄደው 17ኛው ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባዔ ስኬታማ እንዲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ በበኩላቸው÷ በይነ መረብ ከጥቅሙ ባሻገር ከመረጃ መረብ ወንጀሎች፣ ከጥላቻ ንግግሮች እንዲሁም ከሀሰተኛና የተዛቡ ዜናዎች ስርጭት አኳያ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አሉታዊ ጎኖች እንዳሉት ተናግረዋል።

በመጭው ህዳር የሚካሄደው ጉባዔ ኢትዮጵያ እየሠራች ያለውን ሥራ ለዓለም ለማሳየት፣ የኢትዮጵያን ብሎም የአፍሪካን ተሰሚነት ለማሳደግ፣ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ትስስር ለመፍጠር እንዲሁም ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ተመላክቷል፡፡

በዘቢብ ተክላይ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.