Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ምዕራብ ክልል የ2015 ረቂቅ በጀት 11 ቢሊየን 33 ሚሊየን በላይ ሆኖ እንዲጸድቅ ለምክር ቤቱ መራ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት በተከታታይ በካሄዳቸው 8ኛ እና 9ኛ መደበኛ ስብሰባዎች የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
 
ምክር ቤቱ በ8ኛ መደበኛ ጉባዔ በተለያዩ ጉዳዮች የተወያየ ሲሆን÷በዋናነት የክልሉ ብሄረሰቦች ምክር ቤት ስልጣንና ተግባር ለመዘርዘር የወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቷል፡፡
 
ምክር ቤቱ በተጨማሪም የክልሉ የ2015 በጀት ዓመት ረቂቅ ጥቅል በጀት 11 ቢሊየን 33 ሚሊየን 665 ሺ 967 ብር ሆኖ እንዲጸድቅ ለክልሉ ምክር ቤት መርቷል።
 
ከዚህ ባለፈም የቦንጋ ትምህርት ኮሌጅን እንደገና ለማቋቋምና ለማስተዳደር የወጣ ረቂቅ አዋጅ ላይ መስተዳድር ምክር ቤቱ በመጀመሪያ አጀንዳነት የተመለከተው መሆኑ ተገልጿል፡፡
 
በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርተ ማዕቀፍ የቦንጋ ትምህርት ኮሌጅን የሥልጠና ሥርዓት እና ደረጃ በማሻሻል፣መልካም አስተዳደር በማስፈን፣ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት አሰራር ስርዓት ለመፍጠር የቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ እንደገና ለማቋቋምና ለማስተዳደር የሚረዳ የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት በማስፈለጉ ረቂቁ አዋጁ መዘጋጀቱ ተመላክቷል።
 
መስተዳድር ምክር ቤቱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ብዝሃ ዋና ከተሞች ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይም መክሯል።
 
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሕገ መንግስት አንቀጽ 6 የክልሉ መንግስት ብዝሃ ዋና ከተሞች እንደሚኖሩትና ይህም በህግ እንደሚወሰን በተቀመጠው መሰረት የክልሉ መንግስት ብዝሃ ዋና ከተሞች ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱ ተጠቁሟል።
 
መስተዳድር ምክር ቤቱ በቀረቡት ረቂቅ አዋጆች ላይ በዝርዝር ከተወያየና በስፋት ከመከረ በኃላ በመሉ ጽምጽ ለክልሉ ምክር ቤት እንዲተላለፉ መወሰኑን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
 
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.