የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሁለት ዙር ሲሰጥ የነበረው የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና መጠናቀቁን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በሁለት ዙር ሲሰጥ በነበረው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከ 900 ሺህ በላይ ተማሪዎች በ130 የፈተና ጣቢያዎች መፈተናቸው ተጠቁሟል፡፡
ፈተናው በመጀመሪያው ዙር የማህበራዊ ሳይንስ ፈተና ሂደት ካጋጠሙና በመጀመሪያው ዙር ማጠቃለያ ከተገለጹ ችግሮች ውጪ በታቀደው መሰረት በስኬት ተጠናቋል ያለው ሚኒስቴሩ÷ የ2ኛ ዙር ተፈታኞችም ከዛሬ ጀምሮ ወደ የአካባቢያቸው መመለስ መጀመራቸውን ገልጿል።
ዩኒቨርሲቲዎች ለፈተናው ውጤታማነት ያደረጉት ዝግጅት እና በፈተና አሰጣጥ ሂደት ላይ የነበራቸው አስተዎጽኦ ከፍተኛ የነበረ ሲሆን÷ ተፈታኞችም የፈተና ስርዓቱን ባከበረ መልኩ ፈተናቸውን ሲወስዱ ቆይተዋል ተብሏል።
ለዚህም የትምህርት ሚኒስቴር ለወላጆች፣ ለተፈታኝ ተማሪዎች እና ለፈታኝ መምህራን ፣ ለጣቢያ አስተባባሪዎች ፣ለሱፐርቨይዘሮች፣ ለጸጥታ አካላት እና በየደረጃው ለፈተናው ስኬታማነት የበኩላቸውን ለተወጡ አካላት ምስጋና አቅርቧል፡፡
የዘንድሮው የፈተና አሰጣጥ ሂደት የፈተና ስርቆት እና ኩረጃን በማስቀረት ሂደት የነበረው አስተዋጽኦ ውጤታማ መሆኑ የታየበት እንደነበረም ማወቅ ተችሏል ነው ያለው ሚኒስቴሩ።
በቀጣይም የፈተና አሰጣጥ ስርዓቱን በማሻሻል የተሻለ እና በራሱ የሚተማመን ትውልድን ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሰራ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
ሚኒስቴሩ የፈተናውን አጠቃላይ ሂደት በሚመለከት ዝርዝር መረጃዎችን በቀጣይ እንደሚያሳውቅ ተጠቁሟል፡፡