አንጋፋው ድምፃዊ አሊ ቢራ በስራዎቹ ህያው ሆኖ ይኖራል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አንጋፋው ድምፃዊ አሊ ቢራ በምንማርባቸው ስራዎቹ ህያው ሆኖ ይኖራል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡
የአርቲስት ዓሊ ቢራ አስከሬን የሽኝት ሥነ ስርዓት በወዳጅነት ዐደባባይ እየተካሔደ ነው፡፡
በመርሐ ግብሩ የተገኙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ÷ አሊ ቢራ ከምስራቅ ኢትዮጵያ ያገኘነው ፀሃያችን ነው፤ በእርሱ ብዙ አትርፈናል፤ በዓለም ታውቀናል ነው ያሉት፡፡
አሊ ቢራ የፍቅር ሰው ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች እሱንም በተግባር አሳይቶናል ብለዋል በንግግራቸው፡፡
ተወዳጁ አርቲስት የዘፈነውን ኖሮታል፤ ውጤቱንም አይቶታል ያሉት ከንቲባዋ እኛም የምንናገረውን ከኖርን ሀገራችን ትቀየራለች፤ ትፀናለች ብለዋል፡፡
በህይወት ሳለን ትላልቅ ስራዎች ከሰራን አንሞትም ፤ እናርፋለን እንጂ ያሉት ከንቲባ አዳነች፥ አሊ ቢራም አረፈ እንጂ አልሞተም ፤ በምንማርባቸው ስራዎቹ ህያው ሆኖ ይኖራል ብለዋል በመልዕክታቸው፡፡
እንደ አሊ ቢራ አይነት ሰዎችን ማፍራት ላይ ትኩረት አድርገን መስራት ይገባናል ሲሉም ነው የገለፁት፡:
በፌቨን ቢሻው