Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ  የጥምቀት በዓል በሠላም እንዲጠናቀቅ  ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተራና የጥምቀት በዓል በሠላም እንዲጠናቀቅ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከከተማዋ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ጋራ በመቀናጀት የከተራና የጥምቀት በዓል ምክንያት በማድረግ ዛሬ ውይይት አካሂዷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታሁን አበራ÷ የከተራና የጥምቀት በዓላት በሰላም እንዲከበሩ በሁሉም ዘርፍ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል።

በዚህ መሰረትም ቢሮው በከተማዋ የሚገኙ የሰላም ሰራዊት አባላት ከበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሚሰጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኅብረተሰቡም አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲገጥሙ ለጸጥታ ኃይሎች በማሳወቅ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ነው ጥሪ ያቀረቡት።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነጻነት ዳባ በበኩላቸው÷ ሁሉም የሰላም ዘብ መሆን አለበት ብለዋል።

በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ በበዓሉ የሚሳተፉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ አባላት ሥራቸውን ለመከወን የሚያስችላቸው ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

እነዚህ አባላት ከሰላም ማስጠበቅ በተጓዳኝ፤ ሌሎች የተለያዩ የበጎ ተግባር አገልግሎቶችን እንደሚያከናውኑ ጠቁመዋል።

የመድረኩ ተሳታፊ በጎ-ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶች በዓሉ በሰላም እንዲከበር የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸው÷ከወዲሁ የፅዳት ዘመቻ በማከናወን ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ እንደሚገኙ አንስተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.