አባያ እና ጫሞን ለመታደግ ሰፊ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ያሥፈልጋል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሥምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኙትን የአባያና ጫሞ ሐይቆች ከተደቀነባቸው የመጥፋት አደጋ ለማትረፍ ሰፊ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፡፡
በተለያዩ ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ለመጥፋት የተቃረቡት እነዚህ ሐይቆች በዓሳ ምርታቸው እና በመስኅብ ሥፍራነታቸው ይታወቃሉ፡፡
በጋሞ ዞን ደንና አካባቢ ጥበቃ ጽኅፈት ቤት የብዝኃ ሕይወት ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ጋምቡራ ጋንታ ÷ የአካባቢው ነዋሪዎች በሐይቆቹ ዙሪያ እና በመጋቢ ወንዞች አቅራቢያ የሚገኙ ደኖችን ለእርሻ ፣ ለቤት መሥሪያነት ፣ ለማገዶ ፍጆታ እና ለመሣሠሉት አገልግሎቶች ስለሚጠቀሟቸው መሬቱ ገላጣ እየሆነ በመምጣቱ እየደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከፍተኛ መጠን ያለው አፈር እየታጠበ ወደ ሐይቆቹ እየገባ መሆኑንም አብራተዋል።
በደለል የተነሳ የሐይቆቹ ጥልቀት እየቀነሰ ፣ በአንፃሩ ደግሞ ሥፋታቸው እየጨመረ መምጣቱን የጠቀሱት አቶ ጋምቡራ ÷ ችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ ካልተሰጠው የውሃ አካላቱ ከሁለት አሥርት ዓመታት በኋላ ሙሉ በሙሉ የመጥፋት አደጋ እንደሚገጥማቸው አስረድተዋል።
በአካባቢው የተፈጥሮ ሐብት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ እንዲሁም አባያ እና ጫሞ ሐይቆች ከተደቀነባቸው አደጋ ለመታደግ የጋሞ ዞን ደንና አካባቢ ጥበቃ ጽሕፈት ቤት “ፎረስትስ ፎር ፊውቸር” ከተባለ እና የጀርመን የልማት ድርጅት አካል ከሆነ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር በሦስት ወረዳዎች እና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች በድምሩ 970 ሄክታር በሚሸፍን መሬት ላይ የደን ልማት እና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን ማከናወኑን አቶ ጋምቡራ ገልጸዋል።
ፅሕፈት ቤቱ ባለፉት ዓመታት ከ“ፎረስትስ ፎር ፊውቸር” ፕሮጀክት ጋር በመተባበር በጌዣ የተፈጥሮ ደን ዙሪያ ባካሄደው የዛፍ ችግኝ ተከላ እና የአካባቢ ክብካቤ ሥራ 174 ሄክታር የሚሸፍን ሰው ሰራሽ ደን መፈጠሩን ተናግረዋል።
በትብብር በተከናወኑት የአፈር እቀባ እና የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራዎች ወደ ጫሞ ሐይቅ የሚገባውን የደለል መጠን በተወሰነ መልኩ መቀነስ መቻሉንም አስታውቀዋል።
ለአፈር እቀባ ሥራው ከቀርከሃ የሚሰሩ መገደቢያዎችን ጨምሮ ሌሎች አካባቢ በቀል ዘዴዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውንም ነው የተናገሩት።
አቶ ጋምቡራ አያይዘውም ከአካባቢ ጥበቃ እና ደን ልማት ሥራው በተጓዳኝ በቀርከሃ ምርት እና በችግኝ ማፍላት ሥራዎች በስድስት ማኅበራት ለተደራጁ የአካባቢው ነዋሪዎች የገቢ ማስገኛ የስራ ዕድል ተፈጥሯል።
በ“ፎረስት ፎር ፊውቸር” ፕሮጀክት ከታቀፉት ማኅበራት መካከል የሲሶቴ ችግኝ ልማት እና አቅርቦት ማኅበር አባል የሆኑት አቶ ተሾመ ብዙነህ ÷ማኅበራቸው በዚህ ዓመት ብቻ ከ442 ሺህ በላይ ችግኞችን ለገበያ ማቅረቡን ገልጸዋል።
እንደ አቶ ተሾመ ገለጻ የማኅበሩ አባላት በተፈጥሮ ጥበቃ ላይ በንቃት ከመሳተፍ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እያሻሻሉ ይገኛሉ።
በአባያና ጫሞ ሐይቆች ላይ የተደቀነውን የመጥፋት አደጋ ለመቀልበስ እንዲቻል የሚዲያዎች እና ባለድርሻ አካላት በችግሩ ላይ ሰፊ የግንዛቤ ሥራዎችን ሊሰሩ ይገባል ሲሉም አቶ ጋምቡራ መልክታቸውን አስተላልፈዋል።
በወንደሰን አረጋኸኝ