የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ስፖርት ፌደሬሽኖች ለትግራይ ክልል የዘርፉ ተቋማት ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ስፖርት ፌደሬሽኖች ለትግራይ ክልል የዘርፉ ተቋማት ድጋፍ አድርገዋል፡፡
በባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ የተመራ የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ስፖርት ፌደሬሽኖች ልዑካን ቡድን ለሥራ ጉብኝት መቀሌ ከተማ መግባቱ ይታወቃል፡፡
ልዑኩ ከትግራይ ክልል የዘርፉ ተቋማት መሪዎች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል፡፡
ውይይቱን የመሩት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ÷ጉብኝቱ እና ድጋፉ በዋናነት በክልሉ ያሉ ችግሮችን በመረዳት መልካም የሥራ ግንኙነት ለመፍጠር ይረዳል ብለዋል።
የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ለትግራይ ክልል የስፖርት ኮሚሽን እና የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኮምፒውተርን ጨምሮ ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁስ እና የ1 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉ ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለትግራይ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቢሮ ቁሳቁስ እና የ1ሚሊየን ብር ድጋፍ፣ የኢትዮጵያ ውኃ ዋና ፌዴሬሽን ለትግራይ ክልል ውኃ ዋና ፌዴሬሽን የቢሮ ቁሳቁስ እና የ40 ሺህ ብር ድጋፍ እንዲሁም የኢትዮጵያ ዳርት ፌዴሬሽን ለትግራይ ክልል ዳርት ፌዴሬሽን የቢሮ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል ።
በቀጣይ በቁሳቁስ፣ በገንዘብ እና በስልጠና ድጋፍ በማድረግ እና መልካም የሥራ ግንኙነት በመፍጠር በቅንጅት እንደሚሰራ መገለጹንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡