4 ሺህ ከፍተኛ ተሿሚዎች፣ 215 ሺህ አመራሮችና ባለሙያዎች ሃብታቸውን አስመዝግበዋል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ4 ሺህ በላይ ከፍተኛ ተሿሚዎች እንዲሁም 215 ሺህ በላይ አመራሮችና ባለሙያዎች ሃብታቸውን እንዳስመዘገቡ የሥነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የሃብት ማሳወቅና ምዝገባ አሰራር ሥርዓት የተመዝጋቢዎችን የግልጽነትና የተጠያቂነት ደረጃ በማሳደግ ለጸረ-ሙስና ትግል የሚያስገኘው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የመንግስት ከፍተኛ ተሿሚዎች፣ አመራሮች እና ባለሙያዎች እንዲሁም የምክር ቤት አባላት የሃብት መዝገባ ሒደት በዲጂታል አሰራር እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ይህም የሃብት ምዝገባ ሒደቱን ቀልጣፋና ውጤታማ እንዳደረገው የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ በለጠ ብርሃኑ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
በ2015 በጀት ዓመትም ከፌዴራል እና ክልሎች 4 ሺህ 114 ከፍተኛ የመንግስት አመራሮችና ተሿሚዎች፣ 215 ሺህ 735 ባለሙያዎችና አመራሮች ሃብታቸውን እንዳስመዘገቡ ገልጸዋል፡፡
ከተለያዩ ዘርፎች ጥቆማ የቀረበባቸውን አመራሮች የሃብት ምንጭ ትክክለኛነትን የማረጋገጥ እና የጥቅም ግጭትን የመለየት ስራ በአራት ዙር መከናወኑንም ጠቅሰዋል፡፡
በቀጣይ የዲጂታል ሃብት ምዝገባ ስርዓቱን አቅም እና ደህንነት በማሳደግ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል፡፡