የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በክልል ደረጃ ተከበረ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)18ኛውን የብሔር፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በክልል ደረጃ ተከበረ፡፡
“ብዝሃነት እና እኩልነት ለሃገራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል 18ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቴፒ ከተማ ተከብሯል።
በመርሐ ግበሩ የክልሉ የመንግስት ተጠሪና የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጸጋዬ ማሞ ÷ የኢትዮጵያ አርማ የሆነውን የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን ማክበር ኢትዮጵያውያን በልዩነት ውስጥ ያላቸውን አንድነት የሚያጎለብት፣ ይበልጥ የሚያስተዋውቅና የሚያቀራርብ ነው ብለዋል።
እንዲሁም 18ኛውን የብሔር፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በሲዳማ ክልል በሰሜን ሲዳማ ዞን ተከብሯል።
የሲዳማ ክልል አፈ ጉባኤ ፈንታዬ ከበደ እንዳሉት ÷ ኢትዮጵያ በልዩነት የደመቀች፤ በአንድነት የጠነከረች ሀገር እንድትሆን የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ማንነት በእኩልነት ሊከበርና ሊታወቅ ይገባል ፤ ለዚህም ነው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በየዓመቱ የሚከበረው ብለዋል።
በተመሳሳይ የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በአፋር ክልል ደረጀ የክልሉ ርዕስ መስተዳደር አወል አርባ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አሲያ ከማል እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የተለየዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በተለያዩ ሁነቶች በድምቀት ተከብሯል።
18ኛው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተከበረ ሲሆን ÷ በመርሐ ግብሩ የክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በዓሉ የህዝባችንን አብሮነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትልቅ ግብዓት ሊሆነን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
እንዲሁም 18ኛውን የብሔር፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በክልል ደረጃ በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ የተከበረ ሲሆን ÷በመድረኩ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ በዓሉን ስናከብር የህዝቦችን አንድነትና አብሮነት ለማፅናት ቃል የሚታደስበት ዕለት ጭምር ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በቅድስት በርታና በጥላሁን ይልማ ተጨማሪ መረጃ ከየክልሎቹ መንግስት ኮሙኒኬሽን