Fana: At a Speed of Life!

ጠንካራ የሎጂስቲክስ ሥርዓት ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥት የሎጂስቲክስ ዘርፉ በስትራቴጂ እንዲመራና ጠንካራ ሎጂስቲክስ ለመገንባት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ ተናገሩ።

በኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን አዘጋጅነት በኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ዘርፍ መሪ እቅድ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ዲፒ ግሎባል በተሰኘ አማካሪ ድርጅት የተጠና የሎጂስቲክስ መሪ እቅድ ቀርቦ ውይይት እየተካሄደበት ይገኛል፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፥ ሎጂስቲክስ ለሀገር ኢኮኖሚ ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ የዘርፉን እቅድ በየጊዜው መከለስና ማሻሻል ያስፈልጋል።

ሎጂስቲክስን በቴክኖሎጂ ማዘመን፣ ግልፅ አሰራር በመዘርጋት መምራት እንደሚገባ ጠቁመው መንግሥት የሎጂስቲክስ ዘርፉ በስትራቴጂ እንዲመራና ጠንካራ ሎጂስቲክስ ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዛሬው ዕለት ለውይይት የቀረበው መሪ እቅድ የኢትዮጵያ ሎጂስቲክስ ዘርፍ ክፍተቶችን መለየትና የቀጣይ መዳረሻ ለመተለም አይነተኛ ሚና እንዳለው መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በመጀመሪያው ምዕራፍ ጥናት ተልዕኮዎችን ለመለየት፣ በዘርፉ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ለመተግበርና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪንን ለማሳደግ የጋራ አረዳድ ለመያዝ እንደሚያግዝ ገልፀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.