Fana: At a Speed of Life!

ለአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ መረጋገጥ ሕብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ መርማሪ ቦርዱ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልልን ሰላምና ጸጥታ ለማረጋገጥ የሕብረተሰቡ የተቀናጀ ተሳትፎ ወሳኝ ሚና እንዳለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ አመላክቷል።

ቦርዱ ይህንን የገለፀው፥ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ ከባህርዳር የኮማንድ ፖስት ኃላፊዎች እንዲሁም በክልሉ የጸጥታ መደፍረስ ተጠርጥረው በባህርዳር ከተማ አስተዳደር ማረሚያ ቤት ከሚገኙ ተጠርጣሪዎች ጋር ባደረገው ውይይት ነው።

የአማራ ክልል በፖሊቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ዘርፎች ላይ የተሻለ አቅም እንዲገነባ በማስቻል ለጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ከተፈለገ በቅድሚያ የክልሉ ሰላምና ጸጥታን ማረጋገጥ ይገባዋል ሲል ቦርዱ አመላክቷል።

ቦርዱ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ጋር በነበረው ቆይታ፥ በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ ቀን ጀምሮ ቦርዱ የሰራቸውን የተለያዩ ክንውኖች በተመለከተ ገለጻ አድርጓል፡፡

ከተጠርጣሪዎች የሰብዓዊ አያያዝ ሁኔታና የምርመራ ሂደት ዙሪያ መስተካከልና ተጠናክሮ መቀጠል አለባቸው ባሏቸው ጉዳዮች ዙሪያም ተወያይተዋል ነው የተባለው፡፡

ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በዚህ ወቅት፥ የክልሉን ሰላምና ጸጥታ የተሻለ ለማድረግ በተደጋጋሚ ከሕዝብ ጋር የውይይት መድረክ እየተደረገ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ለሰላም ካለው ቁርጠኝነት የተነሳ ለታጠቁ ኃይሎች የሰላምና የምህረት ጥሪ በማቅረብ እንዲሁም ከነዚህ ኃይሎች ጋር ውይይት እያደረገ ይገኛል ሲሉም ነው የገለጹት።

የተደረገው የሰላም ጥሪ በሕገ መንግሥቱ ይቅርታ ከማይደረግላቸው ወንጀሎች ውጭ ከዚህ ቀደም የነበሩ ወንጀሎችን ይቅርታ እንደሚያሰጥም አንስተዋል።

ይህን በመገንዘብም የክልሉ መንግሥት ለሰላም እጁን ከዘረጋ ከየትኛውም ኃይል ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ ነውም ብለዋል።

የቦርዱ ሰብሳቢ አዝመራ አንዴሞ፥ ሲንከባለሉ እና ያደሩ ልዩነቶችና ጥያቄዎች ለመፍታት ከመላው የሀገሪቱ ህዝብ ጋር ለመመካከር ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙንም ነው ያስታወሱት።

ኮሚሽኑ ሕብረተሰቡ የሚያነሳቸው መሰረታዊ አጀንዳዎች በማሰባሰብ ለአጀንዳዎቹ መፍትሔዎችን ለማግኘት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ይህን ተግባር ከግብ እንዲደርስ ጥያቄዎችንና ችግሮችን ለመፍታት እንዲረዳ የምክክር ኮሚሽኑ በክልሉ ገብቶ መስራት እንዲችል መደላድል መፍጠር እንደሚያስፈልግም ነው ያነሱት።

በክልሉ በየደረጃው ሊፈቱ የሚችሉ የተለያዩ ጥያቄዎቸ ቢኖሩም፤ የትኛውንም ጥያቄና ፍላጎት ምላሽ እንዲያገኝ ከተፈለገ የክልሉ ሰላምና ጸጥታ እንዲረጋገጥ ሁሉም ሕብረተሰብ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይገባዋል ብለዋል።

የባህርዳር ኮማንድ ፖስት ኃላፊ ሜጀር/ ጀነራል ሙሉአለም አድማሱ በበኩላቸው ፥ ኮማንድ ፖስቱ በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በዚህ ወቅት ከተያዙ ተጠርጣሪዎች መካከል የተሃድሶ ስልጠና በመስጠትና በመምከር ወደ ሕብረተሰቡ የተቀላቀሉ መኖራቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

በተጨማሪም ለፍርድ የሚቀርቡ ተጠርጣሪዎች ልየታና የምርመራ ሂደት ተጠናቆ ለፍርድ ለማቅረብ እየተሰራ እንደሚገኝ ማንሳታቸውን ከተወካዮች ም/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.