Fana: At a Speed of Life!

የመውጫ ፈተና መመዝገቢያ ጊዜ ወደጥር 20 ተራዘመ

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የትምህርት ሚኒስቴር የመውጫ ፈተና መመዝገቢያ ጊዜ እስከ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም መራዘሙን አስታውቋል፡፡

በ2016 ዓ.ም የመውጫ ፈተና ለመፈተን ተገልጾ የነበረው የምዝገባ ጊዜ ከጥር 8 ቀን 2016 ዓ.ም እስከ ጥር 15 ቀን 2016 ዓ.ም መሆኑ ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ በተፈታኞች ጥያቄ መሰረት የምዝገባ ጊዜው እስከ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም የተራዘመ ሲሆን÷ ሌሎች ሁኔታዎች ግን ቀደም ሲል በተገለጸው አግባብ እንደሚከናወኑ ተገልጿል፡፡

የመውጫ ፈተና በድጋሚ ለሚፈተኑ አመልካቾችም ከ2015 የትምህርት ዘመን ጀምሮ በሁሉም በቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞች ለዕጩ ተመራቂ ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት የመውጫ ፈተና እየተሰጠ ነው ተብሏል፡፡

በ2016 አጋማሽ ላይም የመውጫ ፈተናን ለመፈተን በመጠባበቅ ላይ ላሉ ተፈታኞች በሙሉ ፈተናው ከጥር 27 እስከ የካቲት 1 ቀን 2016 ዓ.ም ይሰጣል መባሉን የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

ስለሆነም በሐምሌ 2015 ዓ.ም የመውጫ ፈተናውን ተፈትነው ላላለፉ እና ከጥር 27 እስከ የካቲት 1 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ የመውጫ ፈተናውን በድጋሚ (Re-exam) ለመውሰድ በመጠባበቅ ላይ ላሉ ተፈታኞች በሙሉ ምዝገባ የሚያካሂዱትና የመፈተኛ ተቋም (የመንግስት ዩኒቨርሲቲ) የሚመርጡት በዚህ ማስፈንጠሪያ (Link) (https://exam.ethernet.edu.et) መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

በዚሁ መሠረትም ከጥር 8 እስከ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ የምዝገባ ክፍያ 500 ብር በቴሌ ብር ብቻ በመክፈል መመዝገብ ይቻላል ነው የተባለው፡፡

ተጨማሪ ድጋፍ የሚፈልጉ አመልካቾችም በስልክ ቁጥር +251 118 13 21 76 ወይም በኢሜይል registration@ethernet.edu.et በኩል ድጋፍ ማግኘት እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ የመውጫ ፈተና የሚፈተኑ ዕጩ ተመራቂዎች ምዝገባ የሚያካሂዱትና የአገልግሎት ክፍያ የሚፈጽሙት በተቋማቸው በኩል መሆኑንም ነው ትምህርት ሚኒስቴር ያስታወቀው፡፡

በተጨማሪም አስፈላጊው የመፈተኛ መረጃዎችም በተቋማቸው አማካኝነት እንደሚደርሳቸው ተመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.