Fana: At a Speed of Life!

በሶማሊያ በኩል የተሰጠው መግለጫ የተሳሳተ ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሊያ በኩል የተሰጠው መግለጫ በሌሎች የአፍሪካ ሕብረት ተሳታፊ ሀገራት መሪዎች ጭምር ተቀባይነት ያለገኘና የተሳሳተ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም (ዶ/ር) ዛሬ በሰጡት መግለጫ÷ ከሶማሊያው ፕሬዚዳንት ጋር በተያያዘ የተስተዋሉ ጉዳዮችን አብራርተዋል፡፡

በዚህም እንደ አስተናጋጅ ሀገር ኢትዮጵያ የሁሉንም ሀገራትና መንግስታት መሪዎችን በቆይታቸው ደ ኅንነታቸውን የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለባት አስገንዝበዋል፡፡

ይሁን እንጂ የሶማሊያ ፕሬዚዳት በመንግሥት የተመደቡላቸውን የፀጥታ አካላት አንቀበልም ብለዋል ነው ያሉት አምባሳደር መለስ፡፡

ይህ አሠራር በመላው ዓለም የተለመደ መሆኑን አንስተው÷ በሶማሊያ ልዑክ በኩል የሆነው ከዚህ በተቃራኒ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ለመጡ ሁሉም ሀገራትና መንግስታት መሪዎች ያደረገውን የክብር አቀባበል ለሶማሊያ ፕሬዚዳንት ማድረጉንም አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ በላይ ግን የሶማሊያ ልዑክ የደኅንነት አባላት የጦር መሳሪያ ታጥቀው ወደ አፍሪካ ኅብረት ለመግባት ሲሞክሩ በኅብረቱ የፀጥታ አካላት ተከልክለዋል ነው ያሉት፡፡

ይህም የሕብረቱን የፀጥታ አካላት የሚመለከት እንጂ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም ብለዋል በመግለጫቸው፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትም ከሕብረቱ ቅጥር ግቢ ደሕነታቸውን ከማስጠበቅ ውጭ በሕብረቱ ቅጥር ግቢ እንዳይገቡም የመከልከል ኃላፊነት የለውም ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

በሶማሊያ በኩል የተሰጠው መግለጫም በሌሎች የሕብረቱ ተሳታፊ ሀገራት መሪዎች ጭምር ተቀባይነት ያለገኘና የተሳሳተ ነው ብለዋል አምባሳደር መለስ፡፡

በመራኦል ከድር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.