የገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር፣ ገበታ ለትውልድ ፕሮጄክቶች የኢትዮጵያን የቱሪዝም ገጽታ በመሠረታዊነት እየቀየሩ ነው- ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመሩ የገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጄክቶች የኢትዮጵያን የቱሪዝም ገጽታ በመሠረታዊነት እየቀየሩ ነው ሲሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ከገበታ ለሸገር እና ገበታ ለሀገር ጋር በተያያዘ ሚኒስትሩ ቀጥሎ የቀረበውን ሐሳብ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አአጋርተዋል፡፡
ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር! የኢትዮጵያን የቱሪዝም አቅም የገለጡ ኢኒሼቲቮች
ኢትዮጵያ በአስደናቂ ታሪኳ፣ በተለያዩ መልከዓ ምድሮች እና ህያው ባህሏ የጉዞ መዳረሻ ሆና ይበልጥ እንድትቀጥል በቱሪዝም መሠረተ ልማት እየታደሰች ትገኛለች።
ከአንድ ድንጋይ ከተጠረቡ የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት ጀምሮ እስከ ጥያ ትክል ድንጋይ፣ ከሶፍዑመር ዋሻ እስከ ጎንደር የነገስታት ግንቦች፣ ከአክሱም ሐውልት እስከ ሐረር ግንብ ወዘተ ያሉ ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና አካባቢያዊ ቅርሶች እና ምልክቶች ባለቤት ናት።
ገና ውሳኔ የሚጠብቁትን ሳይጨምር ኢትዮጵያ በዩኔስኮ 11 የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶቿን በአለም ቅርስነት አስመዝግባለች። በተለይ የገዳ፣ የጥምቀት፣ የመስቀል፣ የጨምበላላ ወዘተ የማይዳሰሱ ቅርሶች አጓጊ የጉዞ መዳረሻ እና ተመራጭ እንድትሆን ረድተዋል።
እነዚህ አቅሞች የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከቱሪዝም በእጅጉ ተጠቃሚ እንዲሆን ያደርጋሉ። የውጭ ምንዛሪ ገቢን ያሳድጋል፣ የአገር ውስጥ ሀብትን በማንቀሳቀስ ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል። እንደ ታዳሽ ኃይል፣ ችርቻሮ እና የምግብ ማቀነባበሪያ ያሉ ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች እንዲስፋፋ ያደርጋል። የግል ፋይናንስ፣ የአቅም ግንባታ እና የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንቶችን በማሰባሰብ ያዋህዳል። ማህበረሰቦችን የሚያጠናክር እና የተፈጥሮ ሃብቶችን የሚጠብቅ ሁሉን አቀፍ፣ አካባቢያዊና አካታች እድገትን ያበረታታል። በትናንትነው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የተመረቀው እጅግ ውብ የሆነው የጎርጎራ ሪዞርትም እነዚህን ውጥኖች ይበልጥ የሚያሳካ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተፀነሰው የገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር፣ ገበታ ለትውልድ ፕሮጄክቶች የኢትዮጵያን የቱሪዝም ገጽታን በመሠረታዊነት እየቀየሩ ናቸው። እነዚህ ኢንሼቲቮች ከቢሮ ወደ ከተማ፣ ከከተማ ወደ ሀገር እየሰፉ፣ ከመሀል ሀገር ራቅ ያሉ የመስህብ ስፍራዎች፣ መልከዓ ምድሮች እና ፓርኮችን በመሠረተ ልማቶች በማስተሳሰር አዳዲስ የቱሪስት እድሎችን እንዲከፈቱ መደላድል እየፈጠሩ ይገኛሉ።
ከዚህ በፊት በመሠረተ ልማት እጦት ከተጓዦች ተደብቀው የቆዩትን መንፈስን የሚያድሱ የመስህብ ስፍራዎችን፣ መልከዓ ምድሮች፣ እጅግ የተለዩ አዕዋፋት እና ዕጽዋቶችን በትስስሩ በተፈጠሩ ዕድሎች ለጎብኝዎችና አሳሾች በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታን እየፈጠሩ ነው። ዕድሜ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢንሼትቮች ኢትዮጵያ በመሠረተ ልማት ኔትዎርክ፣ እጅግ ያማሩ እና የየራሳቸውን አካባቢዎች እና በድምር የሀገር ገጽታን እየቀየሩ ያሉ ሪዞርቶች ላይ ኢንቨስት በማድረግ ተደብቀው የነበሩ እምቅ የመስህብ ስፍራዎችን፣ መልከዓ ምድሮችን፣ ፓርኮችን እና ታሪካዊ ቦታዎችን እየገለጠች ትገኛለች።
የተሻሻለ የቱሪዝም መሠረተ ልማት ለጎብኚዎች ተደራሽነትና ደህንነትን ያበረታታል፤ እንቅስቃሴአቸውን ቀላል ያደርገዋል። የመንገድ መሠረተ ልማት እና የአየር ማረፊያዎችን በማሻሻል በውጭ እንግዶች ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረግ ጉዞን ቀላል እንዲሆን ያስችላል።
ከዚህ አንፃር በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች እየተከናወኑ የሚገኙ የኤርፖርት ማስፋፊያዎች ለዚህ አንፀባራቂ ምሳሌ ነው። በአዲስ አበባ እና ክልሎች የተጀመሩ የኮሪደር ልማቶችም እንዲሁ። በኢትዮጵያ እየተገነቡ የሚገኙ ግዙፍ ግድቦች እና የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫዎች ለቱሪዝም መዳረሻ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዘላቂ ሃይል ለማቅረብ ይረዳሉ።
ኢንሼትቮቹ የአካባቢና ቅርስ ጥበቃ፣ የማህበረሰብ ተሳትፎ፣ የአቅም ግንባታ እና የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንቶችን ያካትታሉ። የአካባቢ ማህበረሰቦችን በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ በማካተት ከቱሪዝም ሁሉንም ማህበረሰብ በአካታችነት መርሆዎቹ ተጠቃሚ ያደርጋሉ። የኢትዮጵያን የበለጸገ የባህል ትሩፋት በመጠበቅ የግሉ ሴክተር በመነቃቃት የማያቋርጥ እድገትን ያበረታታል።
የጀመርነው ጉዞ እልህ አስጨራሽ ቢሆንም ከወዲሁ ትሩፋቶች እየታዩ በመሆናቸው የወደፊቱን ተስፋችንን የሚያለመልም ነው። መንገዳችን መደመር፣ ግባችን ሁለንተናዊ ብልጽግና ነው።