በሲዳማ ክልል በመሬት መንሸራተት አደጋ የ6 ሰዎች ሕይወት አለፈ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሲዳማ ክልል ማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ከባድ ዝናብ ባስከተለው የመሬት መንሸራተት አደጋ የሥድስት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተሰምቷል፡፡
በዞኑ ወንሾ ወረዳ ግሽሬ ጉዱ ሞና ሆሞ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ትናንት በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ህይወታቸውን ካጡ ሰዎች በተጨማሪ በሥድስት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱ ተገልጿል፡፡
ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች የሕክምና ዕርዳታ እያገኙ መሆኑን የገለጸው የክልሉ መንግሥት፤ ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እና የጸጥታ አካላት ወደ ስፍራው ማቅናታቸውን አስታውቋል፡፡
በጠፋው የሰው ሕይወት የተሰማውን ሐዘን ገልጾ፤ ለተጎጂ ቤተሰቦችም መጽናናትን ተመኝቷል፡፡
በሌሎች አካባቢዎችም መሰል ችግሮች ሊፈጠሩ ስለሚችሉ ሕብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስቧል፡፡