ባዕድ ነገር የተቀላቀለበት የምግብ ዘይት ለገበያ አቅርበዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባዕድ ነገር የተቀላቀለበት እና ንፅህናውን ያልጠበቀ ከ200 በላይ ጀሪካን የምግብ ዘይት ለገበያ አቅርበዋል የተባሉ ሦስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ፡፡
ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ውስጥ ነው ተብሏል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ዋሉት÷ ከግለሰቦቹ ላይ ዘይት ገዝቶ ወደ ክልል ከተማ አስጭኖ የተጓዘ ነጋዴ ዘይቱን ለገበያ ሲያቀርብ ትክክለኝነቱን እና ንፅህናውን በመጠራጠሩ በድጋሚ ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስጭኖ በማምጣት ለሸጡለት ግለሰቦች ከመለሰ በኋላ ለፖሊስ በሰጠው ጥቆማ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ፖሊስ የቀረበለትን ጥቆማ ተቀብሎ ባደረገው ክትትል እና በተጠርጣሪዎቹ መጋዘን ውስጥ ባከናወነው ብርበራ 20 ሊትር በሚይዝ ጀሪካን ተሞልቶ የተከማቸ ባዕድ ነገር የተቀላቀለበት እና ንፅህናውን ያልጠበቀ የምግብ ዘይት በኤግዚቢትነት መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡