Fana: At a Speed of Life!

ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የተገነባውና በሰዓት 80 ሺህ ዳቦ የሚያመርተው ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ተመረቀ።

በፋብሪካው ምርቃ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በምረቃው ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ፋብሪካው የዳቦ ፋብሪካ ብቻ ሳይሆን፤ በምግብ ራሳችንን የመቻል ፍላጎታችንን፣ ከድህነት የመውጣት ጥማትን እና የብልፅግና ጎዳናን አመላካች ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ በ10 ወራት ፋብሪካ ገንብቶ ማጠናቀቅ የሚታሰብ አልነበረም፤ በተለይም ለሚድሮክ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ ሚድሮክ ከነበረበት ድክመት ተላቆ ፋብሪካውን በዚህ ፍጥነት ማጠናቀቅ መቻሉ ለሌሎችም ትምህርት የሚሆን ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አክለውም መንግስት በቀጣይ 2 ዓመታት ስንዴን ከውጭ ማስገባት የማቆም ፍላጎት እንዳለው በመግለጽ፤ ለዚህም የሙከራ ምርቶች መጀመራቸውን አስታውቅዋል።

ስንዴ ማምረት ብቻ ሳይሆን ምርቶቹን ወደ አግሮ ኢንዱስትሪ መቀየር አስፈላጊ መሆኑንም የገለፁ ሲሆን፥ ለዚህም ለግሉ ዘርፍ ጥሪ መቅረቡን አስታውቅዋል።

መንግስት ላቀረበው ጥሪ ሼክ መሃመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ፈጣን ምላሽ መስጠታቸውን በመግለፅ፤ የሸገር ዳቦ ፋብሪካም እውን እንዲሆን በማድረጋቸው ምስጋናቸውን ያቀረቡላቸው ሲሆን፥ የኢትዮጵያ መንግስት ሁሌም ከጎናቸው እንደሆነ አረጋግጠዋል።

መሰል የዳቦ ማምረቻዎችን ከአዲስ አበባ ውጪ በክልል ከተሞችም ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን እና ለዚህም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሌሎች ከተሞች መሰል መለስተኛ የዳቦ ፋብሪካዎችን ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሯን አስታውቀዋል።

ተጨማሪም የዱባይ አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ዛይድ አልናህያንም ከፍ ያለ ፋብሪካ ቃል መግባታቸውን እና ይህም በቅርቡ ወደ ስራ የሚገባ መሆኑንም ነው ያስታወቁት።

እነዚህ አሁን የተገነቡ እና ወደ ፊት የሚገነቡ ፋብሪካዎች በቀን ዳቦ ለማግኘት ለሚያዳግታቸው ሕፃናት ዳቦ እንዲያገኙ የሚያስችሉ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

“አዲስ አበባን፣ ክልሎችን፣ ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን እንለውጣለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፤ “ኢትዮጵያ የጀመረችውን በሙሉ ታጠናቅቃለች፤ ይህም በየአደባባዩ እየጮኸች ሳይሆን ሪቫን እየቆረጠች ነው” ብለዋል።

ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማም፦ የሸገር ዳቦ ማምረቻው ተገንብቶ እውን እንዲሆን ለተሳተፉ አካላት መስጋና አቅርበዋል።

የሸገር ዳቦ ፋብሪካ መገንባት የከተማውን ነዋሪዎች የኑሮ ጫና ይቀንሳል ያሉት ኢንጂነር ታከለ፥ በቀጣይም የከተማዋ ነዋሪዎችን ጥያቄ የሚመልሱ ሥራዎችን በማቀድ ወደ ስራ መገባቱብንም አስታውቅዋል።

የሚድሮክ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አብነት ገብረ መስቀል በበኩላቸው፥ ሜድሮክ ኢትዮጵያ ለአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ነዋሪ ህዝብ በከፍተኛ ጥራት እና በተመጣጣኝ ዋጋ ዳቦ አምርቶ ማቅረብ እንዲቻል የሸገር ዳቦ ፋብሪካን ገንብቶ ለፍሬ አብቅቷል ብለዋል።

በ41 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ፋብሪካው፤ የዳቦ እና የዱቄት ፋብሪካ፣ የሻይ ቅጠል ማቀነባበሪያ እና 120 ሺህ ኩንታል ስንዴ ማከማቸት የሚያስችል 4 ጎተራ እንዳለው አስታውቀዋል።

በ6 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው የዳቦ መጋገሪያ ፋብሪካው በሰዓት 80 ሺህ ዳቦ የሚያመርት መሆኑን እና በቀን በሶስት ፈረቃ እስከ 2 ሚሊየን ዳቦ የሚያመርት መሆኑ ገልፀዋል።

የሸገር ዳቦ ፋብሪካ ግንባታ በአጠቃላይ በ900 ሚሊየን ብር ወጪ መከናወኑን ያስታወቁት አቶ አብነት፥ አጠቃላይ ወጪውም በሚድሮክ እህት ኩባንያዎች የተሸፈነ መሆኑንም አስታውቅዋል።

ፋብሪካው ከምርት እስከ ማከፋፈል ሂደት ቁጥራቸው 3 ሺህ 400 ለሚደርሱ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥር መሆኑንም ገልፀዋል።

በሙለታ መንገሻ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.