አቶ አረጋ ከበደ ለቅዱስ መርቆሪዎስ ዓመታዊ ክብረ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በየዓመቱ በድምቀት ለሚከበረው የቅዱስ መርቆሪዎስ ዓመታዊ ክብረ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት “በኢትዮጵያ የታሪክ አውድ ውስጥ ስሟ በደማቁ በሚጠራው ደብረ ታቦር ከተማና በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ መካነ ኢየሱስ በየዓመቱ በድምቀት ለሚከበረው የቅዱስ መርቆሪዎስ ዓመታዊ ክብረ በዓል እንኳን አደረሳችሁ” ብለዋል፡፡
በፈረስ ጉግስ ትርዒት ታጅቦ የሚከበረው የቅዱስ መርቆሪዎስ ክብረ በዓል ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ እና ታሪካዊ ትውፊቱን ጠብቆ በማልማትና በማስፋፋት የልማት ጀግኖች መፍጠሪያ ብሎም ሁነኛ የኢኮኖሚ ምንጭ ለማድረግ በቅንጅት መስራት እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡
በሀገር እና በዓለም አቀፍ የቱሪዝም መድረኮች ላይ የህዝብ የአደባባይ ልዩ ምልክት ሆኖ በጉልህ የሚነሳ አይነተኛ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን በትኩረት መስራት የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡