Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን እና የጣሊያን ጉምሩክ ኤጀንሲ በትብብር እንደሚሠሩ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን እና የጣሊያን ጉምሩክ ኤጀንሲ በሀገራቱ መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት የሚመጥን የጉምሩክ አገልግሎት ለመስጠት በትብብር እንደሚሠሩ ተገለጸ፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ከጣሊያን ጉምሩክ ኤጀንሲ የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር ጀኔራል አንድርያ ማዚላ እና በጣሊያን ጉምሩክ የአውሮፓ እና የዓለም አቀፍ የጉምሩክ ጉዳዮች ኃላፊ ራፋኤል ካፑአኖ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡

በዚሁ ወቅትም ሁለቱ ሀገራት በጋራ ለመሥራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን መረጃ አመላክቷል፡፡

የጉምሩክ አገልግሎት ዓለም አቀፍ እና በርካታ ሀገራትን የሚያስተሳስር መሆኑ በውይይቱ ላይ የተገለጸ ሲሆን፤ ለዘርፉ እድገትም የሀገራት ቅንጅት ወሳኝ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚስተዋለው የንግድ እንቅስቃሴ ፈጣን እና ተለዋዋጭ ባሕሪ ያለው በመሆኑ፤ ይህን ታሳቢ ያደረገ አገልግሎት ለመስጠት እንዲቻል የጉምሩክ ተቋማትን ማጠናከር ይገባል ተብሏል፡፡

የሁለቱ ሀገራት የጉምሩክ ተቋትም በኢትዮጵያ እና ጣሊያን መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት የሚመጥን የጉምሩክ አገልግሎት ለመስጠት በቅርበት እንደሚሠሩ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም ተቋማቱ በቴክኖሎጂ እና በዐቅም ግንባታ ሥራዎች ያላቸውን ልምድ እና ተሞክሮ ለመለዋወጥ የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚሠሩ ተጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.