በደን ልማትና ጥበቃ ዘርፍ የሕብረተሰቡ ተጠቃሚነት እያደገ ነው ተባለ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የደን ሽፋንን ለማሳደግ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት የሕብረተሰቡ ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስታወቀ፡፡
ከደን ውጤቶች ሮያሊት ገቢ እስከዚህ ወር ድረስ ከ27 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የክልሉ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አድማሱ ወ/ማርያም ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡
በ2016 ዓ.ም በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 232 ሚሊየን ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸው የደን ችግኞች መተከላቸውን አስታውሰው፤ የእንክብካቤ ሥራውም ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰዋል፡፡
ለ2017 የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርም 273 ሚሊየን ዓላማ ተኮር ችግኝ ለማዘጋጀት ታቅዶ እስከዚህ ወር ድረስ 245 ሚሊየን መዘጋጀቱን አረጋግጠዋል፡፡
የተዘጋጀው ችግኝም 10 በመቶ ለኢንዱስትሪ ግብዓት፣ 20 በመቶ ለግንባታ አገልግሎት፣ 30 በመቶ ለአካባቢ ጥበቃ እና 40 በመቶ ለማገዶ አገልግሎት እንዲውል ታሳቢ መደረጉን አስረድተዋል፡፡
ከአረንጓዴ ዐሻራ ጋር በተያያዘ በርካታ ሕዝብ በንቃት በማሳተፍ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ የሕብረተሰቡ ተነሳሽነት ማደጉን እና አዳዲስ የደን መሬቶችንም መፍጠር መቻሉን አንስተዋል፡፡
የተለያዩ የተከላ ስልቶችን በመጠቀምም ክልላዊ የደን ሽፋኑን ከነበረበት ወደ 18 ነጥብ 7 በመቶ ለማሳደግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ነው ያስታወቁት፡፡
ከደን ልማት እና ጥበቃ ጋር በተያያዘም ከ46 ሺህ 109 ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
በተለያየ ምክንያት የተራቆቱ መሬቶችን ጨምሮ የተመናመኑ ደኖችን ሕብረተሰቡ በማኅበር ተደራጅቶ እንዲጠብቅና ተጠቃሚነቱን እንዲያሳድግ እየተሠራ ያለው ሥራም ስኬታማ ነው ብለዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው