ከ4 ቢሊየን ብር በላይ የገበያ ትስስር የተፈጠረበት ኤክስፖ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከ4 ቢሊየን ብር በላይ የገበያ ትስስር መፈጠሩን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል አስታወቁ፡፡
ሚኒስትሩ በሦስተኛው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ማምረት የህልውና አጀንዳ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ሀገር አቀፍ የ2017 የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከመካሄዱ አስቀድሞ፤ በክልሎች፣ በዞኖችና በወረዳዎች 168 የውይይት መድረኮች እና 94 የንግድ ትርዒቶች መካሄዳቸውን ገልጸው፤ በነዚህ የንግድ ትርዒቶች 400 ሚሊየን ብር የሚገመት ግብይት መፈፀሙን ጠቅሰዋል።
የሀገር ውስጥ ምርትን ማስፋትና የመጠቀም ባህልን ለማሳደግ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በተከታታይ እየተካሄደ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በኢትዮጵያ ታምርት የ2017 ኤክስፖ በርካታ አምራቾች ምርቶቻቸውን እንዳቀረቡና ከ120 ሺህ በላይ ጎብኝዎች እንደተሳተፉበትም ጠቅሰዋል፡፡
በኤክስፖው ከ4 ቢሊየን ብር በላይ ግብይትና የገበያ ትስስር መፈጸሙን ጠቁመው፤ የዘርፉን ማነቆዎች ለመፍታት የሚያስችሉ የፓናል ውይይቶችም መካሄዳቸውን አመላክተዋል፡፡