ትኩረት የሚሻው የሚዛን ቴፒ ማስተማሪያ ሆስፒታል ደም እጥረት
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሚዛን ቴፒ ማስተማሪያ ሆስፒታል ባጋጠመው የደም እጥረት ምክንያት ለደንበኞች ተገቢውን ህክምና ለመስጠት አልቻልኩም አለ፡፡
ሆስፒታሉ ለቤንች ሸኮ እና አጎራባች ዞኖች እንዲሁም ከጋምቤላ ክልል ለሚመጡ ታካሚዎች አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን÷ ለድንገተኛ ህክምና የሚመጡ ታካሚዎችን ህይወት የማትረፍ ኃላፊነትም እየተወጣ ይገኛል።
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በሆስፒታሉ አግኝቶ ያነጋገራቸው ታካሚዎች ለህክምና ቢመጡም የደም እጥረት በመኖሩ ወረፋ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን አስረድረዋል፡፡
የሆስፒታሉ ስራ አስፈጻሚው ዶ/ር እርቅይሁን ጳውሎስ በሆስፒታሉ የደም እጥረት ማጋጠሙን አንስተው÷ የህሙማንን ደም ፍላጎት ለማሟላት ከአዲስ አበባ፣ ወሊሶ፣ መቱ፣ ጅማ እና ቦንጋ ከሚገኙ የደም ባንኮች ደሙን በማጓጓዝ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
የደም ባንክ በአካባቢው ባለመኖሩ ቀልጣፋ የህክምና አገልገግሎት ለመስጠት እና ህይወትን ለማትረፍ የሚደረገውን ጥረት አስቸጋሪ አድርጎታልም ነው ያሉት፡፡
ጉዳዩን ለሚመለከታቸው አካላት ከማሳወቅ አልፎ የደም ባንክ በሚዛን ከተማ ለማቋቋም ሙከራዎች የነበሩ ቢሆንም ፍቃድ ማግኘት አለመቻሉን ጠቁመዋል፡፡
የቤንች ሸኮ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሄኖክ አባጅፋር የጉዳዩን አሳሳቢነት ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ ለማሳወቅ መሞከሩንና በቀጣይም መፍትሄ እስኪያገኝ ጥረቱን እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ደም እና ኅብረ ኅዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ታዬ ለተቋሙ በሆስፒታሉ በኩል ተደጋጋሚ ጥያቄ መቅረቡን አስታውሰው÷ በቀጣይ ሊደረጉ የሚገባቸውን ድጋፎች ለማድረግ ዝግጁነት መኖሩን ገልጸዋል፡፡
በሆስፒታሉ ላይ ካለበት ጫና እና ከደም ባንክ ማዕከላት ካለው ርቀት አንፃር ታይቶ ማዕከሉ ቢገነባ ለሌሎች ደም ባንክ ማዕከላት የሚደረግ ድጋፍን ሁሉ ለማድረግ ከውሳኔ ላይ መደረሱንም ጠቁመዋል፡፡
በተራመድ ጥላሁን