ፕሬዚዳንት ታዬ መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብርን አስጀመሩ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብርን አስጀምረዋል።
ፕሬዚዳንት ታዬ በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን የደረሰው አደጋ ባስከተለው ጉዳት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸው፤ ለተጎጂ ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝተዋል።
ኢትዮጵያውያን ባህላችን መረዳዳትና መደጋገፍ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ከባህላችን በተቀዳው እንቁ እሴት መሠረት እንዲሁም በተደራጀና ስርዓት ባለው መልኩ ድጋፍና እርዳታ ከሚያረጉ ማዕከላት መካከል መቄዶኒያ ቀዳሚው ነው ብለዋል።
የማህበራዊ ኃላፊነት የመወጣት ትልቅ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ አብዛኛው ስራ የሚሰራው በበጎ አድራጎት ማህበራት በኩል መሆኑን አንስተዋል።
መንግሥት ማህበራዊ ፖሊሲን ጭምር በመንደፍ የዜጎችን ጤናና ልዩ ልዩ መሠረታዊ ጉዳዮችን ለማሟላት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያዊያን ከ9 ሺህ በላይ ዜጎችን ይዞ ድጋፍ ለሚያደርገው መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ድጋፋቸውን እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
መርሐ ግብሩን ከማስጀመራቸው በፊት ማዕከሉን ተዘዋውረው የጎበኙት ፕሬዚዳንት ታዬ እና ባለቤታቸው ፅጌ ሀይሌ ማዕከሉ የሚያከናውነው የበጎ አድራጎት ተግባር ከጠበቁት በላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በመርሐ ግብሩ መጀመሪያ ላይም ከልጃቸው የተላከ 1 ሺህ ዶላር ድጋፍ አበርክተዋል።
የሰዎችን ሕይወት በመታደግ የሚታወቀው ማዕከሉ ከዛሬ መጋቢት 6 ጀምሮ የሚቆይ ታላቅ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት መጀመሩን በይፋ አስታውቋል።
ማዕከሉ እስካሁን ከ9ሺ በላይ ሰዎችን ከጎዳና በማንሳት እየረዳ የሚገኝ ሲሆን፤ በ56 ከተሞች ቅርንጫፎችን ከፍቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
መቄዶኒያን ለመርዳት ለሚፈልጉ ደጋፊዎች በሚከተሉት መንገዶች አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላሉ ተብሏል።
- ባንክ፡ በሁሉም ባንኮች ባለው የሂሳብ ቁጥር 7979 በመጠቀም።
- ስልክ መስመር፡ ወደ 8131 አጭር የፅሁፍ መልዕክት በመላክ ወይም በመደወል።
በተጨማሪም በድርጅቱ ግቢ ውስጥ እንደ ሰርግ፣ ልደት፣ ክርስትና እና መታሰቢያ ያሉ ዝግጅቶችን በማድረግ ደስታንና ትዝታን ከነዋሪዎቹ ጋር ማጋራት እንደሚቻል ጥሪ አስተላልፏል።
በዓለምሰገድ አሳዬ