የሀረማያ እና ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች ያሰለጠኗቸውን ተማሪዎች አስመረቁ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀረማያ ዩኒቨርስቲ ለ71ኛ ዙር በተለያዩ የትምህርትና የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና በሶስተኛ ዲግሪ መርሐ ግብሮች በተለያዩ የሳይንስ፣ የጤና፣ የግብርና፣ የማህበራዊ ሳይንስና በሌሎች የሙያ ዘርፎች የተማሩ 3 ሺህ 320 ተማሪዎችን ነው ያስመረቀው።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጀማል ዩሱፍ(ዶ/ር) እንዳሉት፤ የራስ ገዝ ሽግግር ላይ የሚገኘው ዩኒቨርሲቲው 74ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ ይገኛል።
በመማር ማስተማር ሂደትም የትምህርት ዘርፉን 288 በማድረስ ሀገሪቷ የምትፈልገውን የሰው ሀይል በማፍራት ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 121 ሴቶችን ጨምሮ 418 ተማሪዎች አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው በመደበኛ፣ በተከታታይና በክረምት በተለያዩ መርሃ ግብሮች በመጀመሪያ ዲግሪ እና በሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ነው ያስመረቀው።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ባስተላለፉት መልዕክት፤ ተመራቂዎች በተማሩበት መስክ ህዝባቸውንና ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።
የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ኡባህ አደም (ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የተሰጠውን የመማር ማስተማር ስራ ከማከናወን በተጨማሪ የተለያዩ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።