የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተናን ለመስጠት በቂ ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ከሰኔ 23 ጀምሮ ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና በቂ ዝግጅት ተደርጓል አለ።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት፤ ዘንድሮ 563 ሺህ 501 ተማሪዎች ፈተናውን ለመውሰድ ተመዝግበዋል።
በዚህም ከሰኔ 23 እስከ ሐምሌ 16 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚሰጠው ፈተና የፈተና ጥያቄዎች ደህንነታቸው እና ደረጃቸውን ጠብቀው መዘጋጀታቸውን እንዲሁም ግብዓትን ጨምሮ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።
ፈተናው በበይነ መረብ እና በወረቀት እንደሚሰጥ ጠቅሰው፤ ፈተናውን በበይነ መረብ በ6 ዙር የሚወስዱ ተማሪዎች በሲስተሙ ላይ ልምምድ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የተፈጥሮ ሳይንስ የወረቀት ተፈታኞች በ3ኛው ዙር ከሐምሌ 1 እስከ 3 ድረስ እንዲሁም የማህበራዊ ሳይንስ የወረቀት ተፈታኞች ከሐምሌ 6 እስከ 8 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚፈተኑ ጠቁመዋል።
የተወሰኑ ቦታዎች ላይ በቀድሞው ስርዓተ ትምህርት የተማሩ ተማሪዎች ለመጨረሻ ጊዜ ዘንድሮ ፈተናውን እንደሚወስዱም አመልክተዋል።
ፈታኝ መምህራን እና የፈተና አስፈጻሚዎችን የመመልመል፣ የመመደብ የማሰማራት እና ኦረንቴሽን የመስጠት ስራ ቀደም ብሎ መከናወኑን ገልጸው፤ የፈተና አስፈጻሚዎች ወደ ፈተና ማዕከላት መግባታቸውን ገልጸዋል።
ፈተናውን በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን በትምህርት ሚኒስትሩ የሚመራ የፈተና አስፈጻሚ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በ714 ትምህርት ቤቶች ወይም ማዕከላት ላይ የሚገኙ ከ114 ሺህ በላይ ኮምፒዩተሮችን የመለየት ስራ ተካሂዶ የፈተና ስርዓቱን፣ መሰረተ ልማቱን እና የኃይል አማራጮችን ታሳቢ በማድረግ አሁን ላይ 607 ማዕከላት ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ዩኒቨርስቲዎች፣ ትምህርት ቤቶች እና ኮሌጆችን ጨምሮ በተለያዩ የፈተና ማዕከላት ለሚሰጠው ፈተና ተማሪዎች ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ እና አድሚሽን ካርድ መያዝ እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።
ስማርት ሰዓት፣ የሞባይል ስልክ፣ የጆሮ ማዳመጫ (ኤርፎን)፣ ድምጽና ምስል የሚቀዱ ነገሮችን መያዝ ከፈተና ስለሚያሳግድ አጥብቆ የተከለከለ መሆኑን አስረድተዋል።
በመሳፍንት እያዩ