በኦሮሚያ ክልል በፍትሕ ስርዓቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ2019 በጀት ዓመት በክልሉ በፍትሕ ስርዓቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ከሌሎች የፍትሕ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል አለ።
የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት ጋዛሊ አባሲመል የበጀት ዓመቱን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትና የዕቅድ አቅጣጫዎችን ለጨፌ ኦሮሚያ አቅርበዋል።
በእንቅስቃሴ ላይ ከነበሩ 608 ሺህ 889 መዝገቦች ውስጥ 595 ሺህ 199 መዝገቦች እልባት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ውሳኔ ካገኙት አጠቃላይ መዝገቦች መካከል 585 ሺህ 372 የሚሆኑት በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ እልባት ያገኙ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡
የፍትሕ ሥርዓቱን እሴትና በመጣስ የሥነምግባር ግድፈት በፈጸሙ አባላት ላይ ተገቢ ርምጃዎች መወሰዳቸውንም አንስተዋል።
በክልሉ 2019 በጀት ዓመት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ከሌሎች የፍትሕ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በአቤል ነዋይ