Fana: At a Speed of Life!

እነ እስክንድር ነጋን ጨምሮ 5 ተከሳሾች ላይ ዐቃቤ ህግ ምስክሮቼ ከመጋረጃ ጀርባ ይመስክሩልኝ ሲል ያቀረበውን ጥያቄ ተከሳሾቹ ተቃውመው ተከራከሩ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) እነ እስክንድር ነጋን ጨምሮ 5 ተከሳሾች ላይ ዐቃቤ ህግ ለምስክሮቼ ደህንነት ከመጋረጃ ጀርባ ይመስክሩልኝ ሲል ያቀረበውን ጥያቄ ተከሳሾቹ ተቃውመው ተከራክረዋል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የህገ መንግስት እና የፀረ ሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የተከሳሾች የክስ መቃወሚያ ላይ የዐቃቤ ህግ ምላሽን ለመመልከት ዛሬ በሰጠው ቀጠሮ መሰረት ተሰይሟል።
ዐቃቤ ህግም በክስ መቃወሚያው ላይ አራት ገፅ የጽሁፍ ምላሽ ለችሎቱ ያቀረበ ሲሆን፥ የምላሹ ይዘት በችሎቱ አልተገለፀም።
እንዲሁም ቀጣይ የማሰማቸው ምስክሮቼ ለደህንነታቸው ሲባል በምስክር ጥበቃ አዋጅ መሰረት ከመጋረጃ ጀርባ እንዲመሰክሩልኝ ሲል አመልክቷል።
ተከሳሾችም ከመጋረጃ ጀርባ መባሉ ተገቢነት የለውም ሲሉ መቃወሚያ አሰምተዋል።
የተከሳሽ ጠበቆችም ምስክሩ ማን እንደሆነ የማወቅ መብት አላቸው፣ የምስክሩን ማንነት የማያውቁ ከሆነ እንዲሁም ምስክሩ መስማትና ማየት እንደሚችል ማረጋገጥ ካልቻሉ የመስቀለኛ ጥያቄ ለማቅረብ አያስችልም ብለዋል።
“ፍርድ ቤቱንም ሆነ ችሎቱን እናምነዋለን፣ ነገር ግን ምስክሩ ከመጋረጃ ጀርባ ሲመሰክር ተጨማሪ ሰነድ ይዞ እያነበበ ስለመሆኑ ምንም የምናውቀው ነበር አይኖርም” ሲሉም ተናግረዋል።
እንዲሁም “ምስክሩ በሰውነቱ የሚያደርገውን የሰውነት እንቅስቃሴ ተመልክተን መስቀለኛ ጥያቄ ማቅረብ አለብን፤ ስለዚህ ከመጋረጃ ጀርባ ይመስክሩ ተብሎ የቀረበው ጥያቄ ተገቢነት የለውም” ሲሉ ተከራክረዋል።
ዐቃቤ ህግም በመቃወሚያው ላይ ምላሽ ልስጥ ሲል ፍርድ ቤቱን የጠየቀ ቢሆንም፤ “ላቀረብከው አቤቱታ ምላሽ የሰጡ በመሆኑ ለመልስ መልስ እድል አልሰጥህም” ሲል ፍርድ ቤቱ ምላሹን ገድቦታል።
በተያያዘ ፍርድ ቤቱ በችሎቱ ያልተገኙ 6ኛ እና 7ኛ ተከሳሾችን ከዚህ በፊት የፌደራል ፖሊስ አፈላልጎ ለዛሬ እንዲያቀርብ የታዘዘውን ትዕዛዝ ባለማቅረቡ የፌደራል ፖሊስ ምርመራ ክፍል ኃላፊ ለምን አፈላልጎ እንዳላቀረበ በቀጣይ ቀጠሮ ቀርቦ እንዲያስረዳ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
5ኛ ተከሳሽ የክስ መቃወሚያ ያላቀረቡ በመሆኑ የክስ መቃወሚያቸውን በጽሁፍ እንዲያቀርቡ እና ዐቃቤ ህግም መልሱን ለጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ አዟል።
ችሎቱም በአጠቃላይ ዛሬ የተነሳውን ክርክር ጨምሮ ብይን ለመስጠት ለህዳር 29 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
አቶ እስክንድር ነጋ “በምርጫ መሳተፍ ስለምንፈልግ ችሎቱ ለሁለት ተከፍሎም ቢሆን የተፋጠነ የፍትህ አገልግሎይ ይስጠን፤ ለምርጫው ቅድሚያ መዘጋጀት ስላለብን ይታይልን ሲሉ አቤቱታ አቅርበዋል።
ፍርድ ቤቱም “አቤቱታችሁን ለአስተዳደር በጽሁፍ አቅርቡ” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.