በኦሮሚያ ክልል በኢንቨስትመንት የተሰማሩ የቻይና ኩባንያዎች ለኦሮሚያ ክልል የኮቪድ መከላከያ የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል በኢንቨስትመንት የተሰማሩ የቻይና ኩባንያዎች ለኦሮሚያ ክልል የኮቪድ መከላከያ የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ፡፡
ድጋፉን የለገሱት በኢትዮጵያ የቻይና የንግድ ዘርፍ ማህበራት ከቻይናዎቹ ጂያንግሱ እና ኒንሲያ ሁይ ጋር በመተባበር ነው፡፡
ድጋፉ የኮቪድ መከላከያና የህክምና ቁሳቁስ ማለትም 350 ሺህ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ፣ 20 ቬንትሌተር፣ 4 ሺህ የህክምና ባለሙያዎች የኮቪድ 19 መከላከያ አልባሳትና የመሳሰሉት ያካተተ ነው፡፡
ድጋፉን የተረከቡት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ቻይና ሁልጊዜም ከጎናችን ነች፤ የኢትዮጵያና የቻይና ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ ይሄዳልም ብለዋል፡፡
አቶ ሽመልስ አብዲሳ ለተበረከተው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው የቻይና ባለሀብቶች በክልሉ ተጨማሪ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጠይቀዋል፡፡
በድጋፍ ርክክቡ ላይ የቻይና ኤምባሲ የኢኮኖሚ እና የንግድ ጉዳዮች ሚኒስቴር አማካሪ የድርጅቶቹ ተወካይ ሊ ዩ ተገኝተዋል፡፡
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መንግስቱ በቀለ ድጋፉ እየጨመረ የመጣውን የኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከል እንደሚውል ገልጸዋል፡፡