የሩስያና የቱርክ ፕሬዚደንቶች በአሸባሪነትና በወሳኝ ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ እየመከሩ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩስያ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን እና የቱርኩ አቻቸው ረጅብ ጣይብ ኤርዶኻን በሩሲያ ከተማ ሶቺ ተገናኝተው አሸባሪነትን በጋራ መዋጋት በሚችሉባቸው እና በሌሎች ቀጠናዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ምክክር እያደረጉ ነው፡፡
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ወሳኝና ወቅታዊ በተባሉ ጉዳዮች ላይ የሚያደርጉት ውይይት ዓላማ በቀጠናው ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ሊሆን ይችላል ሲሉ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
ወቅታዊው የሶሪያና የአፍጋኒስታን ጉዳይ አንዱ የውይይት አጀንዳቸው መሆኑም ተነግሯል፡፡
ፕሬዚደንት ኤርዶኻን በአሜሪካ የሚደገፍ ነው ያሉትን በሶሪያና በአፍጋኒስታን የሚካሄደውን የሽብር እንቅስቃሴ በሚመለከት ከሩሲያው አቻቸው ፑቲን ጋር ለመምከር ጭምር ነው ወደ ሩስያ ያመሩት።
በቀጣናው ያለውን የአሸባሪዎች እንቅስቃሴ ለመዋጋት ከሩስያ ጋር ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር እንደሚገባም ነው በቱርክ በኩል የታመነበት።
ሁለቱ መሪዎች በሩስያዋ ሶቺ ከተማ እያካሄዱት ባለው ውይይት በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎቻቸው ዙሪያ ጥልቅ ውይይት ማካሄድ ጀምረዋል።
በአሜሪካ የሚመራው የሰሜን አትላንቲክ አገሮች የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል የሆነችው የቱርክ ፕሬዚደንት ለአገራቸው መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፥ በአሁኑ ጊዜ አሜሪካ አሸባሪነትን መዋጋት ሲገባት በግልጽ “የአሸባሪ ድርጅቶች ድጋፊ ሆናለች” ነው ያሉት።
ለአብነትም ህገ ወጥ የሆነው የኩርድስታን ሠራተኞች ፓርቲ አፍቀሪ የሆነውንና በሰሜን ሶሪያ የሚንቀሳቀሰውን ዋይፒ ጂ የተሰኘውን ቡድን አሜሪካ ትደግፋለች በማለት አስረድተዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በመንግስታቱ ድርጅት 76ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የተገኙትን የሁለቱን አገሮች መሪዎች በጎንዮሽ የተናጠል ውይይት ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆናቸው በአገራቱ መሪዎች ላይ ቅሬታ መፍጠሩንም ነው የመገናኛ ብዙሃን መረጃዎች የሚጠቁሙት።
ቱርክ ለሚሳይል መከላከያ የሚውሉ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ከሩሲያ የገዛች ሲሆን፥ በቀጣይም ሌሎች መሳሪያዎችን እንደምትገዛ አስታውቃለች።
ፕሬዚደንት ኤርዶኻን በቅርቡ ለንባብ በበቃውና የመሰረታዊ ለውጥ አቀንቃኝ በሆነው መጽሐፋቸው፥ በተወሰኑ አገራት ፍላጎት የሚመራውን የተባበሩት መንግስታት “የተሻለ ፍትህ የሰፈነበት ዓለም” ማድረግ እንደሚያስፈልግና እንደሚቻል በአጽንኦት መግለፃቸው ይታወቃል።
ምንጭ፡- አር ቲ እና አልጄዚራ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!