Fana: At a Speed of Life!

ጎንደር ለጥምቀት በዓል የሚመጡ እንግዶቿን ለመቀበል ዝግጅት ጀምራለች

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሐመድ በውጭ ለሚኖሩ አንድ ሚሊየን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ በጎንደር ከተማ በሚከበረው የጥምቀት በዓል የሚታደሙ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት ተጀምሯል።
የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዘውዱ ማለደ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያደረጉት ወደ ሀገር ቤት ጥሪ የከተማዋን የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ የሚያነቃቃ ነው።
በተለይም ጥንታዊቷና ታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ በታላቅ ድምቀት ለምታስተናግደው የጥምቀት በዓል መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል በኮቪድ-19 ወረርሽኝ፥ ካለፈው ዓመት ወዲህ ደግሞ በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ሳቢያ የከተማው የቱሪዝምና የኢንቨሰትመንት ፍሰት ተቀዛቅዞ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡
በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተደረገውን ጥሪ ተከትሉ በልዩ ሁኔታ የሚከበረው የጥምቀት በዓል፥ ለቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ፍሰት መጨመርና ለከተማዋ መነቃቃት ምቹ እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡
የከተማው አስተዳደር ጥሪውን ተቀብለው ወደ ሀገር ቤት ለሚመጡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለኢንቨስትመንት የሚውል መሬት ከሶስተኛ ወገን ነፃ አድርጎ በማዘጋጀት ከወዲሁ እየጠበቀ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
”የዘንድሮውን የጥምቀት በዓል በድምቀት ለማክበር ከተማ አስተዳደሩ አንድ ዐቢይና ዘጠኝ ንኡሳን ኮሚቴዎችን በማዋቀር ከወዲሁ ወደ ስራ ገብቷል” ያሉት ደግሞ የከተማው ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ ቻላቸው ዳኘ ናቸው፡፡
በዓሉ በጎንደር ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መንገድ በየዓመቱ በታላቅ ድምቀት እንደሚከበር አስታውሰው÷ “በዓለም በማይዳሰሱ ቅርሶች መመዝገቡ ደግሞ የውጭ ቱሪስቶችን ቀልብ ለመሳብ አስችሎታል” ብለዋል፡፡
ከበዓሉ ቀደም ብሎም የቱሪዝም ፍሰቱን ለመጨመር ያለመና የአካባቢውን ባህል፣ ወግና እምነት እንዲሁም ትውፊቶች የሚያስተዋውቅ የባህል ፌስቲቫል እንደሚካሄድም ሃላፊው ተናግረዋል፡፡
የከተማውን የንግድ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት የንግድ ትርኢትና ባዛርን ጨምሮ የከተማውን የኢንቨስትመንት አማራጮች የሚዳስስና የሚያስተዋውቅ ሲምፖዚየም እንዲሁም የጉብኝት መርሐ ግብር እንደሚዘጋጅም አመላክተዋል፡፡
በበአሉ ለሚታደሙ የሀይማኖቱ ተከታዮችና መሪዎች እንዲሁም ለእንግዶች ማረፊያ እየተመቻቸ መሆኑን ተናግረዋል።
ታዳሚዎች የጥምቀት በዓሉን በቀጥታ ስርጭት የሚከታተሉበት ሁኔታም እንደሚመቻች ነው የገለጹት።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከሚኖሩባቸው ከተሞች በቀጥታ ወደ ጎንደር አየር ማረፊያ ለሚያደርጉት በረራ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ወደ ጎንደር በየቀኑ የሚደረጉ በረራዎችን ቁጥር ለመጨመር እንዲቻል ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመነጋገር ሁኔታዎችን የማመቻቸት ስራ እንደሚከናወን ተገልጿል።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.