Fana: At a Speed of Life!

የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይን እንዲመረምር የተሰየመው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ቡድን እንዲፈርስ ጥያቄ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አደረጃጀት አባላት ጥምረት በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይን እንዲመረምር የተሰየመው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ቡድን እንዲፈርስ ጠየቁ።
 
ጥያቄውን ያቀረቡት በመላው ዓለም የሚገኙ አስራ ሰባት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አደረጃጀት አባላት ጥምረት ሲሆኑ ÷ ጥያቄውንም ለተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነርና ለተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ምክር ቤት አባል ሀገራት ነው ያቀረቡት።
 
ጥምረቱ ይህን ጥያቄ ያቀረበው ቡድን በፈረንጆቹ መስከረም 22፣ 2022 ባወጣው ሪፖርት ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ለማቅረብ በጻፉት ደብዳቤ አማካኝነት መሆኑም ታውቋል።
 
በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማጣራት የኢትዮጵያ የፍትሕ ስርዓት ነጻነቱ ሊጠበቅለትና አቅሙ ሊገነባ እንደሚገባ ሰኔ 1፣ 2014 ዓ/ም በጻፉት ተመሳሳይ ደብዳቤ መጠየቃቸውን አስታውሰዋል።
 
ባለፈው አንድ ዓመት በኢትዮጵያ ላይ በመሰንዘር ላይ ያሉ ያልተገባ ጫናን መፍጠር ታሳቢ ያደረጉ ግፊቶች ሊቆሙ እንደሚገባ ጠይቀው ÷ በዚህ ሂደት በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምክር ቤትም የፖለቲካ መሳሪያ በመሆን ከአባል ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ማበላሸት እንደማይገባው አስገንዝበዋል።
 
ገና ከጅምሩ የኢትዮጵያ መንግስት ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር የወሰዳቸውን ተጨባጭ እርምጃዎችን በደብዳቤያቸው ዘርዝረዋል።
 
በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይን እንዲመረምር የተሰየመው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ቡድን የተቋቋመበት እሳቤ በተሳሳቱ መነሻዎች ላይ የተመሰረተ ነው ያለው ጥምረቱ የተቋቋመው ቡድን ሊፈርስ ይገባል ብሏል።
 
ለዚህ ጉዳይ የተመደበው የህዝብ ሀብትም የኢትዮጵያን የፍትሕ አካላት ለማጠናከር ውሎ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል የተባሉ የአማራና አፋር ክልሎች ምርመራም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል።
 
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ቡድን እንደተጠበቀው የፖለቲካ ዓላማ ያለውና ከደረጃ በታች የሆነ፣ የጉዳዩን አሳሳቢነት የማይመጥንና አንድን ወገን ብቻ ለይቶ ማጥቃትን ዓላማ ያደረገ አደገኛ የሆነ ሪፖርት ይዞ መውጣቱን ገልጸዋል።
 
አባል ሀገራት ይህን የተሳሳተ ሰነድ በፊርማቸው ከማጽደቅ እንዲቆጠቡም ነው ጥምረቱ የጠየቀው።
 
አባል ሀገራት በኢትዮጵያ የተጀመረውንና ለተጎጂዎች ዘላቂ ፍትሕ ለማስገኘትና ጥበቃ ለማድረግ የተጀመረውን ሂደት ሊደግፉ ይገባል ሲሉም ጠይቀዋል።
 
ሁሉም አባል ሀገራት ሙያዊ ስነ-ምግባርን ያልተከተለ፣ ያልተሟላ፣ ለአንድ ወገን ያደላና ፖለቲካዊ ዓላማን ያነገበውንና ቡድኑ ያቀረበውን ሪፖርት ውድቅ እንዲያደርጉና ኮሚሽኑንም እንዲያፈርሱ መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል ።
 
አባል ሀገራት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅርበት በመስራትና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትን በማክበር የፍትሕ ስርዓቱ አቅም እንዲገነባ በአማራ፣ አፋርና በትግራይ ክልሎች ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኝነት እንዲመረምሩ የኢትዮጵያን ፍትሕ አካላት እንዲያግዙ ጠይቀዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.