በኦሮሚያ ክልል ከ8 ሚሊየን በላይ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በመኸር እርሻ ከ8 ሚሊየን በላይ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
በቢሮው የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ሙስጠፋ ሁሴን እንደገለፁት÷ ለ2015/16 የምርት ዘመን በክልሉ 8 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።
ከዚህም ዋና ዋና ሰብሎችን ጨምሮ ከ265 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱን አንስተዋል፡፡
በእስካሁኑ ሒደትም 8 ሚሊየን 90 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር መሸፈኑን ነው ያስረዱት፡፡
የአፈር ማዳበሪያ እጥረትን ታሳቢ ያደረጉ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው÷ በተለይም ደጋማ አካባቢዎች የአፈር ማዳበሪያ ቅድሚያ እንዲደርሳቸው መደረጉን ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡
በዚህም ስንዴ፣ ገብስ፣ የጥራ ጥሬ በሰብሎችን ጨምሮ በዘር መሸፈኑን እና ምርጥ ዘርም ለአርሶ አደሩ በወቅቱ እንዲደርስ ሰፊ ስራ መከናወኑን አመልክተዋል።