ከ2 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር በላይ በሆነ መሬት ላይ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ይከናወናል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 በጀት ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር በላይ በሆነ መሬት ላይ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ እንደሚከናወን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው በሁሉም ክልሎች እንደሚከናወንና እስካሁንም የተወሰኑ ክልሎች የተፋሰስ ልማት ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ማካሄዳቸውን በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፋኖሴ መኮንን ጠቁመዋል፡፡
በዝግጅት፣ በትግበራ እና በማጠቃለያ ምዕራፍ በተለዩ ከ11 ሺህ በላይ ተፋሰሶች ላይ ከ2 ሚሊየን 250 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡
በዝግጅት ምዕራፍ የእርሻ መሣሪያዎችን የማዘጋጀት፣ የባለሙያዎችና አርሶ አደሮች የአቅም ግንባታ ሥራ እና ተፋሰሶችን መለየትና በተፋሰሶቹ ላይ የማቀድ ሥራ መከናወኑን አቶ ፋኖሴ አብራርተዋል፡፡
የቅድመ ዝግጅት ምዕራፉ መጠናቀቁን ተከቶሎም በክልሎች ከጥር ወር ጀምሮ የማስጀመሪያ መርሀ ግብር እየተከናወነ መሆኑን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።
የአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ሲዳማ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች የዘንድሮ የተፋሰስ ልማት የማስጀመሪያ መርሀ ግብር በማከናወን ሥራውን እንደጀመሩ አመላክተዋል፡፡
በትግበራ ሥራውም የተለያዩ ሥነ አካላዊ የአፈርና ውሀ ጥበቃዎችን ማለትም እንደ እርከን፣ የተራራ ላይ ውሃ መያዣ ቦዮችን እና የችግኝ መትከያ ጉድጓዶችን የማዘጋጀት ሥራ እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
16 ሚሊየን 338 ሺህ በላይ ሴቶችን ጨምሮ በአጠቃላይ እስከ 40 ሚሊየን ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረው፤ ተሳትፎው በገንዘብ ሲተመን ከ30 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚሆን ጠቅሰዋል።
ከዚህ ጎን ለጎንም ባለፉት ዓመታት ለተሰሩ ሥነ አካላዊ የአፈረና ውሀ ጥበቃ ሥራዎች እድሳት የሚደረግበት እና የተተከሉ ችግኞችም እንክብካቤና የፅድቀት መጠን ልየታ እንደሚከናወን አያይዘው ገልፀዋል፡፡
በታምራት ቢሻው