Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ የክልሎች የጎንዮሽ የእርስ በእርስ ግንኙነት ለማጠናከርና የሚከሰቱ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት በአዳማ ከተማ ስልጠና ሰጠ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)የፌዴሬሽን ምክር ቤት የክልሎች የጎንዮሽ የእርስ በእርስ ግንኙነት ለማጠናከርና የሚከሰቱ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ከሰሜን እና ምዕራብ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች ለተወጣጡ ባለሙያዎች በአዳማ ከተማ ስልጠና ሰጥቷል።

የአማራ፣ የትግራይ፣ የአፋር፣ የኦሮሚያ፣ የሱማሌ፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝና የጋምቤላ ክልሎች ከፍተኛ ባለሙያዎች ስልጠናው ላይ ተሳትፈዋል።

ስልጠናውን በይፋ የከፈቱት የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ፀሃፊ አቶ ወርቁ አዳሙ ፤ በአንድ አገር ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲረጋገጥ፣ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ልማት እውን እንዲሆን፣ በአጠቃላይ ሁለንተናዊ ብልፅግና እንዲመጣ ከሁሉም በላይ በሀገራችን ሰላም መስፈን ያለበት ሲሆን ሰላም እንዲሰፍንም በክልሎች መካከል የመንግስታት ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።

የመንግስታት ግንኙነት በከባቢው የሚከሰቱ አለመግባባቶችን በውይይት፣ በድርድርና መተማመንን በሚያሳድግና በሚያጎለብት መልኩ ለመፍታት እንደሚያስችል ገልጸው፤ የመንግሥታት ግንኙነት አቅምን ለመገንባትና መልካም ከባቢያዊ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ የጋራ ፕሮጀክቶችን፣ ፕሮግራሞችን በመተግበር የከባቢውን ማህበረሰብ የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል።

የመንግስታት ግንኙነት የሚመራበት የታወቀና ውጤታማ የአሰራር ስርዓት አለመዳበር እንደችግር ሲነሳ የቆየ ቢሆንም፤ አሁን ግን የመንግሥታት ግንኙነት የሚመራበት ራሱን የቻለ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ መውጣቱን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ አዋጅ በተቀመጠው የአሰራር ስርዓት መሰረት እቅዶችን ተግባራዊ ማደረግ እንደሚገባም የቋሚ ኮሚቴው ጸሃፊ አቶ ወርቁ አብራርተዋል።

በመጨረሻም ተሳታፊዎች በክልላቸውና በአጎራባች ክልሎች የሚታዩ ችግሮችን በጥናት መለየት፣ የጥናትን ውጤቱን መሰረት በማድረግ ችግሮችን ለመፍታት ማቀድ፣ እቅዱን የሚያስፈፅም ተቋም መመስረትና የክትትልና ድጋፍ ስራዎችን መስራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡

የጋራ ፎረም ላልመሰረቱ አጎራባች ክልሎች ከዚህ ስልጠና በኋላ ተቋሞቻቸውን መስርተው በጋራ ይሰራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.